Page 9

Page 9 – START

1050 -1280 AD ሁነቶች ሁሉ በኢትዮጵያ ከፍተኛ መሬቶች፣ በሰሜናዊና በመሃከላዊው ተራራማ ቀበሌዎች ላይ የተወሰኑ ነበሩ። በአንፃሩ እስላም ወደ ደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ በመስፋፋት ተራራማውን አካባቢ የያዘውን ንጉሣዊ መንግሥት ከበበው። ገና በ11ኛው መክዘ መጀመሪያ ላይ፣ ባንዲት ቢንት ማያ የተባለች መሪ የነበረው አንድ የተጠናከረ ሞሐመዳዊ ፖለቲካዊ ግዛት ተመሥርቶ እንደነበረ አንዳንድ ተባራሪ የዓረብ ታሪካዊ ሰነዶች ይጠቁማሉ። 45፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

የኢትዮጵያው ክርስቲያናዊ መንግሥት አደረጃጀት፣ በአንድ ፖለቲካዊ መሪ የበላይነት የተማከለና በተጨባጭም ይሁን ለይስሙላ በርሱ ሥልጣን ሥር የሆኑ ልዑላንና ባላባቶች ያሉት አንድ ወጥ ተቋም ሲሆን፣ በአንፃሩ የእስላማዊ ሱልጣናዊ ግዛቶች በአንድ የተማከለ ሥልጣን ስር አልነበሩም። ሱልጣናዊ የቀበሌ መንግሥቶች እርስ በርሳቸው ይዋጋሉ፣ ከነዚህ አንዱ አሸንፎ የበላይነቱን ሲይዝ ጥረቱ ሁሉ ማዕከላዊ ሥልጣን ለመፍጠርና የቀሩትን አንድ አድርጎ ለመያዝ ሳይሆን፣ የበላይነቱን ለመጠበቅ ብቻ የሚያልም ነበር። ከዚህም የተነሳ በያንዳንዱ የሱልጣን ወይም የአሚር ግዛት ውስጥ የማያቋርጥ ውስጣዊ ትግል ይካሄድ ነበር። 45፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

በክርስቲያናዊት ኢትዮጵያና በሱልጣናዊ የቀበሌ መንግሥታት መካከል የነበረው ፉክክር ለረጂም ጊዜ የዘለቀና ብዙ ደም ያፋሰሰ ጦርነት አስከትሏል። የእስላማዊው ወገን ዓላማ፣ በተራሮች የተመከተውን ክርስቲያናዊ ጠላት ባለበት አጥሮ ለመያዝና ለንግድ እንቅስቃሴው በጣም ተፈላጊ የሆኑ ነገሮች በገፍ ከሚገኙበት ከደቡባዊ አውራጃዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ለመቁረጥ ነበር። እነዚህ አውራጃዎች ተፈጥሮአዊ ገፅታቸው የመገናኛ መንገዶችን ለመዘርጋት አመችና፣ የመሃልና የሰሜናዊ ከፍታዎችን ከባሕር ጠረፍ ጋር አገናኝዎች ናቸው። ሁለቱም ወገኖች ደቡባዊ አውራጃዎችን የሚፈልጓቸው እንደዚህ ያለ ኤኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ስለሆኑ ነው። 46፣የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

ይህ ተቃራኒነት የግድ ባህላዊ ልዩነቶችን ማጠናከሩ የማይቀር ነው። ቀደም ሲል እንደ ተወሳው ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመሃከለኛው ባሕር አገሮች ሥልጣኔ ጋር የተሳሰረ ነው፣ በንጉሣዊው መንግሥት ደቡባዊ ምሥራቅ የባሕሩን ጠረፍ ይዞ የሚኖረው የሱልጣናዊ ግዛቶች ሕዝብ ደግሞ ትስስሩ ከእስያና ከአፍሪካ አገሮች እስላም ጋር ነው። 46፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

1279 AD በ13ኛው መክዘ ላይ፣ የሸዋው ሱልጣናዊ መንግሥት በሌሎች ሱልጣናዊ ግዛቶች ሁሉ የበላይነቱን ይዞ ነበር። በሸዋው ሱልጣናዊ ግዛት የበላይነቱን የጨበጠው ወገን፣ በዘልማድ የዘር ግንዱን ወደ ኋላ ቆጥሮ ከመካ የሚነሳው፣ የማሕዙሚ ሥርወመንግሥት ወገንና፣ በ7ኛው መክዘ ላይ ሶሪያን ያቀናው መሪ ተወላጅ ነው። በራሳቸው በሱልጣናዊ ግዛቶች መካከል ግን የማያቋርጥ ትግልና ግጭት ይካሄድ እንደነበረና፣ አንዳንዴ ግዜ ሞሐመዳዊ ገዢዎች ከጠላቶታቸው እየሸሹ ከኢትዮጵያ ቤተመንግሥት ገብተው ይደበቁና ዕርዳታ ይጠይቁ እንደነበር ይታወቃል። በማሕዙሚ ሥርወመንግሥት ውስጥ በተካሔደ የሥልጣን ትግል ላይ፣ ደልጋሚስ ዙፋኑን የቀማው ሱልጣን ድልማራህ ኢብን ማልዛራህ፣ በ1279 ከይኩኖ አምላክ ቤተመንግሥት መጥቶ ዕርዳታና ጥገኝነት እንደጠየቀ ይታወቃል።

1285 AD በዚያን ወቅት በሱልጣናዊ ግዛቶች መካከል ከተደረጉት ዋና ዋና ጦርነቶች አንዱ፣ በሸዋው የማሕዙሚ ሥርወመንግሥትና በይፋቱ የወላስማ ሥረወመንግሥት መካከል የተካሄደው የሥልጣን ትግል ነው። የሸዋው ሱልጣናዊ መንግሥት ለዙፋን በሚደረጉ ውስጣዊ ትግሎችና ፣ በተለይ በ1277 እና በ1280 ዓ.ም. በተደረጉት የወላስማ ወረራዎች በመዳከሙ፣ በ1285 የበላይነቱን ቦታ አጠቃልሎ ለይፋቱ ለቀቀ። ክዚህን ጊዜ አንስቶ የይፋት ሱልጣናዊ መንግሥት ለሶስት መቶ ዓመታት የበላይነቱን ይዞ ቆየ። ከዚህ በኋላ በሁለቱ ታላላቅ ተቀናቃኞች፣ በክርስቲያናዊውና በእስላማዊው ወገኖች መካከል ያለው ግንኙነት እየተበላሸ ሄደ። 47፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

ክርስቲያናዊው ንጉሣዊ መንግሥት ወሰን ለማስፋት ፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ፣ በደቡብና በምሥራቅ ጠርዝ ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች፣ የሱልጣን ግዛቶችን ለአደገኛ ጎረቤት መከታ እንደሆኑአቸው አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። ስለዚህም ወደ እስላም ጎራ እየገቡ ኃይሉን ሊያጠናክሩት በቅተዋል። በዚህን ወቅት ላይ ይፋት ብቻ ሳይሆን አዳል፣ ደዋሮ፣ ባሌ፣ ሃዲያና ፈጠጋር የሞሐመዳዊ ወረዳዎች ነበሩ። ጠንካሮች ናቸው የማይባሉት፣ ከይኩኖ አምላክ በኋላ የተነሱት መሪዎችም ያራምዱት የነበርው ለዘብተኛ ፖሊሲ ለእስላም ኃይል መጠናከር አስተዋፅዖ አድርጓል። 47፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

1314 AD ወጣቱና ታታሪው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አምደ ጽዮን፣ ስመ መንግሥቱ ገብረ መስቀል፣ ነገሠ። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የክብር ቦታ ያለው ሰው ነው። በሳይንሳዊ ጥናት ውስጥ ዘመነ መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን፣ የዚያን ጊዜው ጥበበ ቃላትም በርሱ ስም ነው የሚጠራው። ቀዳማዊ አምደ ጽዮን የመንግሥቱን ድርጅታዊ አንድነትና የንጉሠ ነገሥቱን ሥልጣን የማጠናከሩን ሥራ ተያያዘው። መንፈሳዊው ክፍል ከማንም በላይ የተማረውና እጅግ ተደማጩ ክፍል በመሆኑና፣ ለቤተ ክርስቲያንም ያለውን ኤኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅም በማየት በዚህ ሥራ ላይ ሙሉ ተሳታፊ ሊሆን በቅቷል። “ክብረ ነግሥት” እና “ሥራተ መንግሥት” ብቻ ሳይሆኑ፣ ሌሎች ብዙ ድርሳናትና የጥበበ ቃላት ሥራዎች፣ ዓለማዊና መንፈሳዊ መጻሕፍት የዳበሩበት ወቅት ነበር። የሸዋው የጋስቻ ገዳም መነኩሴ አባ ጊዮርጊስ በ አምደ ጽዮን ዘመን የኖሩ ታዋቂ ሰዎች ናቸው። 56፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

በቀዳማዊ አምደ ጽዮን ዘመን፣ ቤተክርስቲያን በ ኤኮኖሚ ከንጉሠ ነገሥቱ ነፃ ሁኖ የቆመና ከርሱ ቀጥሎ ታላቁ ኤኮኖሚያዊ ኃይል ሲሆን፣ በመንግሥቱም ውስጥ እጅግ ከፍ ያለ ስፍራ ነበረው። ስለዚህም ነገሥታቱ መንፈሣውያኑን ይዘው፣ እንዲያውም ብዙ ጊዜ የነርሱን ትዕዛዝ ተከትለው ለምስተዳደር ይገደዱ ነበር። በፖለቲካውም ራሳቸውን ከቤተክርስቲያን ለማግለል የሞከሩ አንዳንድ ነገሥታት መጨረሻቸው አያምርም ነበር። 49፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ፣ በወደፊቱ የሀገሪቱ ዕድል ላይ ጭምር ወሳኝ የሆነ የተለያየ አመለካከት ያላቸው፣ በትንሹ ሦስት የመንፈሳውያን ስብስቦች ነበሩ። ከነዚህም አንዱ የሀይቅ መነኮሳት ስብስብ ነው። የተከበረው የአቃቤ ሰዓቱ ሹመት በነሱ እጅ ስለ ነበር፣ በንጉሠ ነገሥቱ ውሳኔ ላይ ቀጥታ ተፅዕኖ የማድረግ ዕድል ነበራቸው። ሁለተኛው የሸዋው የደብረ አዝቦ ገዳም መነኮሳት ስብስብ ነው። እነዚህ የእጨጌነቱ ሹመት ድርሻቸው ስለሆነ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ ገዳማት ላይ ሁሉ የበላይ አዝዥነት ሥልጣን ነበራቸው። በመጨረሻም ሶስተኛው ስብስብ በስተ ስሜን በኩል ሀም (ሺመዛ) ላይ የሚገኘው የደብረ ሊባኖስ ስብስብ ነው።

በ14ኛው መክዘ ሁለተኛ አጋማሽ ውስጥ፣ ከዚህ ከፍ ብሎ ከተጠቀሱት የመንፈሳውያን ስብስቦች በቀር አንድ ሌላ ተጨማሪ ኃይል ብቅ አለ። ይህ ማህበረ መነኮሳት የደብረ ቢዘን ገዳም ነው። አቀማመጡ በጣም የሰጠ በመሆኑ (ከዛሬዋ አስመራ አካባቢ ነው)፣ ከምፅዋ ወደ ደባረዋ የሚያልፈውን የንግድ መስመር ይቆጣጠራል። ከዚህም ጋር ለክርስቲያኑ መንግሥት ሰሜናዊ ወሰን የግንባር ምሽግ ነበር። ከፍ ብሎ ከተራሮች ውስጥ የተተከለው ደብረ ቢዘን፣ የኤኮኖሚያዊና ስትራተጂያዊ ጥቅሞች የተቋጠሩበት ቦታ ነው። ሲጀመር ጀምሮ ከባሕር ጠረፍ ሙስሊሞች ጋር በሚያደርጋቸው ትግሎች ስሙ የተጠራ ነበር። ኋላም ደብረ ቢዘን ከዳህላክ ደሴቶች ገዥዎች ጋር በተመሠረተው የወዳጅነት ግንኙነት፣ ኢትዮጵያ ከባሕር ጠረፍ ጋር ለምታከናውናቸው ተግባሮች ወደር የሌለው ጠቃሚ ተቋም ሆኖ አገልግሏል። 52፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

1325 AD ግብፅም በኢትዮጵያ የጠላትነት ፖሊሲ ነበረው። ከዚህም የተነሳ ቀደም ሲል እንዳደረገው ሁሉ፣ አምደ ጽዮንም የዓባይን ወንዝ እገድባለሁ ሲል ግብፅን አስፈራርቷል። ለኢትዮጵያና ግብፅ ግንኙነት መበላሸት ዋና መንስዔ ሁኖ የኖረው በዚያን ጊዜ፣ ከዚያን በፊትና ኋላም ለረጂም ጊዜ፣ ክርስቲያናዊ መንግሥት ከእስክንድርያው የክርስትና መሪ ጋር የነበረው ትስስር ነው። ከኢትዮጵያ ወደ እስክንድርያ የሚሄዱ የንጉሠ ነገሥቱ መልዕክተኞች የግድ በእስላማዊው ግዛት ውስጥ ማለፍ ስለሚኖርባቸው፣ ብዙ ጊዜ ይታገዳሉ፣ ይታሠራሉ፣ ይገደላሉ። ከእስክንድርያ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ፓትሪያርኮችም ተመሳሳይ ዕጣ ይገጥማቸው ነበር። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ለአያሌ ዓመታት ያለ አቡን የምትቆይበት ጊዜ ነበርና በመንግሥቱ ውስጣዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ ከባድ ችግር ያስከትል ነበረ። 60፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

1335 AD አምደ ጽዮን በዚህ ወቅት ያገኘው ድል፣ እስከ ዘመነ መንግሥቱ ፍፃሜ ድረስ በሱልጣናዊ ግዛቶች ላይ የበላይነቱን ይዞ እንዲዘልቅ አስችሎታል። ስለዚህ መሪ የተያዘው መዋዕለ ዜና በአመዛኙ በሱልጣናት ላይ ያካሄዳቸው ጦርነቶችን በስፋት የሚገልፅ ነው። እንደዚሁም በጥንት አማርኛ በዘፈን መልክ ተቀርጾአል።… ከ1331 – 1445 ያሉት ዓመታት በሃገሪቱ ደቡባዊ ምዕራብ ጠርዝ ከሚገኙ እስላማዊ ሱልጣናት ጋር ያላቋረጠ ጦርነት የተካሄደባቸው ዘመናት ናቸው። ለበላይነት የተደረገው ትግል በ1285 ዓም በይፋቱ ሱልጣናትና በወላስማው ዲናስቲ ድል አድራጊነት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ እስላማዊ ኃይሎች መሰባሰብ ይጀምራሉ። ከንጉሣዊው መንግሥት መጠናከር ጎን ለጎን የሱልጣን ግዛቶችም እያበቡ ይሄዳሉ። የሁለቱ ተፃራሪ ወገኖች ውስጣዊ መደርጀት፣ የመስፋፋትና ከፍ ያለ የኤኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውን የደቡባዊ ምሥራቅ ግዛቶችን የመቆጣጠር ምኞት ስለፈጠረ፣ በሁለቱ መካከል የትጥቅ ትግል አይቀሬ እየሆነ መጣ። 59፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

Page 9 – END

Comments are closed.