የተዘጋጀው ለማን ነው?
ይህ ማህበረሠባዊ የፕሮጀክታችን ክፍል ዕድሜ፣ ጾታ፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት፣ ማህበረሰብ፣ ሥፍራ፣ እና የመሳሰሉት ሰብዓዊ መገለጫዎችን ሳይለይ ከታች እንደተጠቀመጠው በ9 ክፍለዓለማት በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የሚያሣትፍ የጋራ መድረክ ነው ፡፡
የዚህ መድረክ ዓላማዎች ምንድን ናቸው?
የዚህ መድረክ ዓላማ የሚከተሉት ሁሉ ናቸው። ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በግለሰብ ደረጃም ሆነ እንደ ማህበረሰብ በየአሉበት በኑሮአቸው እንዲደጋገፉ ለማድረግ። በወገናዊና አለኝታዊ ፍቅር፣ በቀና የትብብር መንፈስ ለመቀናጀት። እንዲሁም ሕዝባዊ ዕድገት ላይ ያተኮረ አዲስ የመረዳጃ ማህበራዊ መድረክን እንደ ባሕላዊ ተቋም አድርጎ ለመፍጠርም ነው።በዚህም መሠረት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተሻለ ግለሰባዊ የኑሮ ጥራት ደረጃን ለማግኘት እንድንችል፣ እርስ በእራሳችን በመተጋገዝ በብቃት እያንዳንዳችን ወደምንፈልገው ከፍተኛ የኑሮ ጥራት አቅጣጫና ደረጃ ከፍ ለመደራረግ፣ ቋሚ የማህበራዊ ትስስር ግንኙነት እንደ ብረት ሠንሠለት ተያይዞ የሚኖር መረብ መሆን እንዲችል። በበጎና ነፃ ትብብር ላይ ተመሥርቶ ተዛማጅ የሆነ ባህላዊ ዕሳቤና ተቋም በየአለንበት ለመፍጠር። የራሳችን ወገን ዓለም አቀፋዊ ጥራትና ብቃት ይዞ በዓለማችን የትም ስለሚገኝ አንዱ ለሌላው ወገኑ የዕውቀት፣ የልምድና የብቃት ኃይል ምንጭ እንዲሆንና እንዲያጎለብተው አመቺ መንገድ በመፍጠር በከፍተኛ ኢትዮጵያዊ አንድነት ስሜት ተነሳስተን ኑሮአችንን በየአለንበት እንድናሻሻል ይረዳ ዘንድ ነው። ዓላማችን እነዚህ ብቻ ናቸው።
ከተሳታፊዎች ምን ይጠበቃል?
ሁላችንም ተሳታፊዎች በተወዳጁ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት፣ መልካም ሥነምግባር፣ ፈርሀ እግዚአብሔር፣ የሕሊና ተገዢነት፣ ሀቀኝነት፣ ክብር፣ የወገናዊ ተቆርቋሪነት፣ ጥበበኛነት፣ በነፃ ብሔራዊ የትብብር አገልግሎትን የመስጠት መንፈስ ተሞልተን እና በፕሮጀክቱ ከፍተኛ ዓላማ እንዲሁም ጥቅም በማመን መሣተፍን ይጠበቅብናል።
ኢትዮጵያዊ አንድነት ፍቅርና ዕድገት ለዘላለም ይለምልም!!!