Community core-value of
the season
LEADERSHIP
የዕውነተኛ መሪ እና አመራር መገለጫ ባህርያት፥
በዚህ ወቅት ዕሴቱ የተመረጠበት ምክንያት፥ በዚህ ወቅት ይህ ዕሴት የተመረጠበት ምክንያት በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያዊው ማህበረሰብ ብዙ የህይወት ተግዳሮቶችና ጉዳቶች የዚህ ዕሴት ትክክለኛ ትርጉምና ዕጦት በኢትዮጵያ ጎልቶ ስለሚታይና ከዚያ አኳያ የዕሴቱን ትርጉም ብዥታ ለማጥራት ዕገዛ ለማድረግ ነው።
ማንኛውም ሰው በራሱ መንገድ መሪ ነው። ሰው የራሱን ኑሮ ወይም ህይወት ከመምራት ጀምሮ፣ ቤተሰቡን፣ ጓደኞቹን፣ የሥራ ወይም የማንኛውም ዓይነት የቡድን እንቅስቃሴ ተሳትፎ ውስጥ ሲኖር ደግሞ ቡድኑን ወይም ድርጅቱን፣ እስከ አገር መሪና አመራር ድረስ ውጤታማ የመምራት ብቃት ላይ የሚደርሰው በመሪነት ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ የላቀ ፣ እንዲሁም ብቃቱ በሌሎች ዓይን በተመራጭነት ቅቡልነት ሲኖረው ነው። ዕውነተኛና በሌሎች ዓይን ተመራጭ መሪ ታማኝና የሚመራቸውም አካላት ላይ ነፃና ገለልተኛ አካል ወይም ተቋም ሆነው እንዲሠሩ የሚያደርግ በዚህም ደረጃ ተፈላጊውን ዕምነት የሚጥልና ውክልና መስጠት የሚችል፣ በመልካም ሥነምግባርና የሞራል ልዕልና በተላበሱ ህዝባዊ ራዕዮችና ዕሴቶች የሚመራ፣ ለሚመሩት አካል ቅንነት አክብሮት እና ፍቅር ሳያጎድል ሁሌም ግልፅ የቃላት መግባባትን የሚመርጥ፣ የቆመለትን ዓላማ በፅናትና ዓርአያነት ሁሌም በተግባር የሚያሳይ፣ በሥሩ ለሚሠራውና ላልተሠራው ጭምር ሁሉ ሙሉ ኃላፊነትን የሚወስድ በዚህም ዋጋ ቢያስከፍልም ዋጋ ለመክፈል ትሁት ዝግጁና ፈቃደኛ የሚሆን፣ የሚመራውን አካል በኃይል ሳይሆን በራሱ በተመሪው ከፍተኛ ተነሳሽነት ተመሪው አካል ትልቅ ሥራ እንዲሠራ አነቃቅቶ የሚያነሳሳ፣ ይህንም ለማደረግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችንና ህግጋትን የሚያስቀምጥ፣ ህግጋቱንም ሁሉ በመጀመሪያ ራሱ አክብሮ ከዚያም በፍትሃዊነት የሚያስከብር፣ ዕውነተኛ መሪ ማለት የመሪው የሥራ ትኩረት የሚመለከተው ስለ ተመሪው አካል አገልግሎት የማግኘት ጉዳይ ብቻ እንጂ በፍጹም ስለመሪው ተገልጋይነትና ግላዊ ግቦች ጉዳይ እንዳልሆነ የተቀበለ መሪና አመራር ሲሆን ነው። በአጠቃለዩ፣ ዕውነተኛ መሪ እና አመራር የሚመራውን አካል ራዕይ እንጅ የራሱን ግላዊ ራዕይ ሊያስፈፅም እንደማይገባ ጠንቅቆ የተረዳና የተቀበለ ባህርያትን ይይዛል።
ለምሳሌነት ማሳያው ከዚሁ ዓውድ እንድአየነው ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ የዕውነተኛ መሪ እና አመራር መገለጫ ባህርያትን በሚገባ የተላበሱ ምርጥ ኢትዮጵያዊ እንደነበሩ ነው። አቡነ ጴጥሮስ የመንፈሳዊ ህይወት መሪ ብቻ ሳይሆኑ፣ የዓለማዊ ህይወትን ለሚኖረውም የዘመናቸው ኢትዮጵያውያን የዕውነተኛ መሪ እና አመራር መገለጫ ባህርያትን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳይተው አልፈዋል። ቀጥሎ ባለው ዓውድ አቡነ ጴጥሮስ የተመረጡበት ምክንያት እንደተጠበቀ ሆኖ ስለ ዕውነተኛ መሪ የተሰጠውን ትርጉም ሁሉ የተሟላ የሚያደርጉ መሪ ነበሩ እላለሁ። ዘሪሁን ተመስገን