Page 1

የሶስት ሺ ዓመታት የኢትዮጵያ ታሪክ በጊዜ መስመር ላይ 

መግቢያ 

ጥንታዊ የግብፅ የፅሁፍ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩትና በሌሎች ተመራማሪ ሊቃውንትም እንደታመነበት፣ የዛሬይቷ ኢትዮጵያና ኤርትራን ያማከለ “የፑንት ምድር” ወይም “የኩሽ አገር” ወይም ከጥናትዊ ግብፅ ጋር ሲተያይም “ደቡብ” በመባል በፈርዖናውያኑ ጭምር የታወቀች፣ ከአምስት ሺህ አምታት በላይ በቆየ መልኩ ግብፅ፣ ኢትዮጵያና የዛሬዋ ኤርትራ መካከል ጠንካራ የንግድ ገበያና ሽርክነት እንደነበራቸው ታሪካዊ ማስረጃዎች ይመሰክራሉ። የዝሆን ጥርስ፣ የተለያዩ እንስሳትና ቆዳቸው፣ የአውራሪስ ቀንድ፣ የኤሊ ቀፎ፣ ወርቅ፣ ዕንቁ፣ ሚይርህ፣ ዕጣን፣ ቅመማ ቅመሞች፣ የምግብ ሰብል ዓይነቶች፣ ጨውና ለባርነት አገልጋይ ህዝቦችን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ወይም ግብፃውያኑ እንደሚሉት ደግሞ “የፑንት ምድር” ወደ ግብፅ፣ እንደ አዱሊስና ዘይላ ባሉ የቀይ ባህር ወደቦችን እና በሌላኛው አቅጣጫ ደግሞ የአባይን ወንዝ ራሱን የቻለ የንግድ መመላለሻ ጎዳና በማድረግ በንግድ ላይ የተመሠረተ የጥንታዊ ኢትዮጵያ አካል የሆነ የሥልጣኔ ዘመንን አሳልፈዋል። እነዚህ ጥንታዊ የንግድ እንቅስቃሴዎች የአፍሪካ ቀንዱ መልክዓምዳራዊ አቀማመጥን ማዕከላዊ ያደረጉ ነበሩ። በቀይ ባሕር ላይ ንግድ፣ ዕውቀትና ሥልጣኔን ይዘው የሚመላለሱ መርከቦች በአንድ በኩል የደቡብ ዓረቢያ፣ ህንድና የሩቅ ምሥራቅ አገራት የህንድ ውቅያኖስን መግቢያና መውጫ በር ሲያደርጉ፣ በሌላኛው በስተሰሜን በኩል ደግሞ ሜዲትራኒያን ባሕርን መናኸሪያው ያደረገው የመካከለኛው ምሥራቅና አውሮፓውያን አገራት የአፍሪካ ቀንዱን የንግድ መተላለፊያ ዋናው መንገዳቸው ላይ ተቀምጦ የሚገኝ ማዕከል ሆኖ አግኝተውታል። ይህም ማለት በቀይ ባሕር ላሉ ደሴቶች፣ በቀይ ባሕር ዳርቻ ላሉ ወደቦችና ውስጣዊ ከተሞቻቸው በኩል ጥንታዊው የኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝብ ለሥልጣኔና ሁሉም ዓይነት ውጪያዊ ዕድሎችና ክስተቶች እንዲጋለጥ አድርጓል።

አጠቃላይ ሥፍራው፣ በግሪክ ሮምና ሌሎች አውሮፓውያን ዘንድ ይህ ከኑብያ፣ ድዓማትና አክሱም ገናና ዘመን ጀምሮ ባሉት ወቅት በአፍሪካ የኢትዮጵያ ግዛት በመባል በአጠቃላዩ የታወቀው ምድር ከዛሬዎቹ ግብፅና ሊቢያ በስተደቡብ ጀምሮ ያለውን ሙሉ የአፍሪካ ቀንድ ምድርን ይዞ እስከ ዛሬዎቹ ታንዛኒያ ገደማ ድረስ የዘለቀ በአንድ የጋራ ኢትዮጵያ በሚል የወል ስም ይጠራ የነበረ ሰፊ ምድር ነው። የንግሥተ ሳባ ምድራዊ ግዛትም ይህ በቀይ ባሕር ዳርቻ ጨምሮ ያለውን ኢትዮጵያና ደቡብ ዓረቢያን ጭምርም ነበር።  ከንግሥተ ሳባ በኋላም፣ እንደዛሬውም ዘመን የየትኛውም አገር ነገሥታትና ሥርዓተ መንግሥታት ሁሉ፣ በየወቅቱ ሁነቶች በተቀያየሩ ጊዜ የግዛቶች መስፋትና መጥበብ አብሮ የሚከሰት ክስተት ነበረ። ከሳባና ኑብያ ወደ ድዓማት፣ ብሎም እስከ አክሱማዊው መንግሥት ባለው የኢትዮጵያ ሃገረመንግሥት ጉዞ ላይ የኑብያ ኢትዮጵያዊው ምድር በግብፅ ፈርዖኖች መዳፍ ውስጥ በቅኝ ግዛት የተያዘ፣ አንዳንዴም ከግብፆች ነፃ ወጥቶ ግብፅን መልሶ ለመግዛት የበቃበት ወቅት ነበር። ፈርዖኖቹ የጥንታዊ ኢትዮጵያ አካል የነበረችውን ኑብያና ጥንታዊ ከተሞቿን ከርማ፣ ናፓታ እና መርዌን ጨምረው ሲገዙ ኢትዮጵያ ተብሎ ከሚጠራው አንድ ምድራዊ ግዛት ላይ ወስደው ነበር። ቀጥሎም ግን በቀጣይ ትውልድ እንደ ፒያንኪ እና ታርሐቃ ባሉ ኢትዮጵያውያን የኑብያ ነገሥታት ግብፃዊ ፈርዖኖች ተገርስሰው የኑብያ ኢትዮጵያውያኑ የግብፅ ሃያ አምስተኛው ሥርወ መንግሥት በመባል ታውቀው ለሰባ አምስት ዓመታት ገደማ ግብፅን ገዝተው ማለፋቸውን ታሪካዊ ማስረጃው ዘግቦታል። በንፅፅር፣ ይህም እንደገና ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአምስተኛው ክፍለዘመን በአክሱም የነገሠው ካሌብ የተባለው ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ቀይ ባሕርን ተሻግሮ ዛሬ የመን የሆነውን የደቡብ ዓረቢያን ምድር በወረራ አስገብሮ እንደገዛ በተመሳሳይ ሁኔታ ታሪክ ከአስቀመጠው ጋር ተመሳሳይ ክስተት ሆኖ ይገኛል።

ከእነዚያ ከመሳሰሉት ጊዜያትም ጀምሮ፣ በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥትና የሥርዓተ መንግሥት ረጂም የምሥረታ ሂደትም፣ አቅጣጫ ቀያሪና ዘዋሪ የሆኑ ብዙ ሕዝባዊ ክስተቶች፣ ፍልሰቶችና ሠፈራዎች በውህደት ተከስተዋል። ኑብያና ሌሎች የጥንታዊ ኢትዮጵያ የግዛት አካላት ከሔዱት ቢቆጠሩም፣ የሃበሻ ምድር በመባል የሚታወቀው ሕዝብና ወገኖቹ ግን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በስም ሆነ በይዘት በዘመናት መካከል ይዞ እየተጓዘ ከድዓማት ወደ ሳባውያንና አክሱም፣ ከአክሱም ወደ ዛጉዌ፣ ከዛጉዌ በይኩኖ አምላክ አስቀጣይነት እስከ ዘመነ ኃይለሥላሤ፣ ከዚያም ወደ ደርግ፣ ከደርግ ደግሞ እስከ ዘመነ ኢህአደግ ድረስ ቀጥሎ ሥነ መንግሥታዊ ስሙንና ተቋሙን ይዞ እስከ አሁኑ የብልፅግና ፓርቲ ሥርዓተ መንግሥት ድረስ መጥቶኣል።

የመንግሥታዊና ሃገራዊ ግንባታ ሂደቱ ሁሌም የሚካሄደው በየዘመኑ ከሚከሰቱ የፖለቲካ ሥልጣንን ተቆጣጥረው የአገረ መንግሥት ምሥረታ ሂደቱን አቅጣጫ ቀያሪና ዘዋሪ ወይም ተፅዕኖ ፈጣሪ በሆኑ መሪዎች አመካኝነት ነው። እነዚህ መሪዎች በየጊዜው ከነባሩ ሕዝብ ዘንድ በከፊል ቅቡልነትና ኢትዮጵያዊ ውህደትን በማረጋገጥ የሚያስቀጥሉ፣ ኢትዮጵያዊ ሀገረ መንግሥት ምሥረታን ያሳለጡ ለየዘመናቸው ስኬታማ መሪዎች ወይም ሥርዓቶች ናቸው። መሪዎቹ ከባዕድም ሆነ ከጎንዮሽ የሚመጡ ሃሳቦችን፣ ዕምነቶችን እና ሕዝቦችን ተቀብለው በማስተናገድ በኢትዮጵያዊነት ስም የሚያዋህዱም ነበሩ። የአይሁዳውያንን፣ የዓረቦችንን፣ የአውሮፓውያንን፣ የህንድና ሩቅ ምስራቆችን እንዲሁም የጎረቤት አፍሪካውያንን ፍለሰትና ውህደትን ኢትዮጵያ በስኬት ስታስተናግድና ኢትዮጵያዊነትን ስትገነባበት ቆይታለች። በዕምነትና ባህልም ረገድ ኢትዮጵያ የአይሁድ ፣ ክርስትና እና እስላም ዕምነቶችን ተቀብላ የዓለማችን ሶስት ታላላቅ ጥንታዊ ሀይማኖቶችን የራሧ አድርጋለች። በዘር ገመድም ቢሆን ከጅምሩ የካምና ሴም ነገዶችን እያዋሃደ መጥቶ፣ በተለይም ዛሬ የሃበሻ ሕዝብና አገር በመባል ለቆየው ውህድና ቅይጥ ሕዝብ በዛሬው ኢትዮጵያዊነት ላይ የመሠረታዊ ሥሪቱ አስኳል ሆኖ ሊታይ በቅቷል።

የኢትዮጵያን ታሪክ ከመጨረሻው 3ሺ ዓመታት ብቻ ጀምረን ስናይ፣ ተወደደም ተጠላ የንግሥተ ሳባና ንጉሥ ሠለሞን ትርክት አይተኬ መነሻው ሆኖ ተቀምጧል። ከመካከለኛው ምሥራቅ የተነሳው በቀዳማዊ ሚኒሊክ ምክንያትነት የአይሁዳውያን ወደ ምድረ ኢትዮጵያ መፍለስ እንደ ማሳያ በኢትዮጵያ ከመጀመሪያዎቹ አንዱ ነበር። ይህም በኋላ ላይ የቤተ እሥራዔላውያን ወይም የፈላሾች የወደ ኢትዮጵያ የተደረገ ፍልሠትና ውህደት ታሪክ አካል ሆኖ እናገኘዋለን። ዛሬ ቤተ እስራዔላውያኑ እናት አገር ወደሚሉት እስራዔል በከፊል ሂደው ቢኖሩም፣ እነዚያ አይሁዳውያን ዕምነታቸውን ይዘው ከነባሩ ኩሻዊ ነገድ ጋር በመቀላቀል ለዘመናት በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የኢትዮጵያዊነትን አገረ መንግሥት ግንባታ መሥራች አካል ሆነው መሠረት ጥለዋል። ቀጥሎም ከደቡብ ዓረቢያ የተነሱት በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ የነገደ ዮቅጣን የሴም ዘርነት ያላቸው ዓረቦች በአዶሊስ፣ አክሱምና ሌሎች የቀይባህር ዳርቻና ውስጣዊ ሥፍራዎችን የንግድ ማዕከላትን መሰረት አድርገው ኖረዋል። እነዚህም መጤ ፈላሽና ተዋሃጅ የደቡብ ዓረብ ሕዝቦች በውህደታቸው ኢትዮጵያዊነትን ከአዳበሩ አካላት መሀል ከዋነኞቹ አንዱ ሆነው አልፈዋል። ሕዝባዊም ባይሆኑ ከዓረቦች መካከልም የተገኙ ሌሎች ብዙ ተፅዕኖ ፈጣሪ አውሮፓውያን፣ የአርመኒያ፣ ህንድና፣ የእስያ ዜጎችም በውህደታቸው ኢትዮጵያዊነትን ከአዳበሩ አካላት መሀል ነበሩ። እንደማሳያ የአክሱም ነገሥታት በግሪክ ቋንቋ ዕውቀታቸው በጣም የተካኑ መሆናቸው የአውሮፓውያን መጤዎችን ታቃፊነት ጭምር ማሳያ ሊሆን ይችላል። ከዚያ ብዙ ቆይቶም ደግሞ፣ በግራኝ አህመድ ጦርነት ማግስት በ16ኛው ክፍለ ዘመን፣ ራሱን ከነገደ ኩሽ የሚመድበው የኦሮሞ ጎሳና ህዝብ ከበረይቱማና ቦረን ከሚባል ከዛሬው ሶማሊያ፣ ኬንያና ኢትዮጵያ ድንበር ገደማ ተቀላቀለ።  ባልተቋረጠ የጥቂት መቶ ዓመታቶች ፍልሠት በዛሬይቷ ኢትዮጵያ ዘመቻ በሚመስል መልክ በተስፋፊነት ውስጣዊ የኢትዮጵያ ግዛቶችን በመጤነት ሠፍሮ ዛሬ የሚገኝባቸውን ግዛቶች ሁሉ ላይ ኢትዮጵያዊነትን የራሱ አድርጎ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በኢትዮጵያዊ ውህደት ውስጥ ለመገኘት በቅቷል። ምናልባትም ከቦረና አና በረይቱማ በስተቀር፣ ከ13 ኛው ክፍለዘመን በፊት በዛሬይቷ ኢትዮጵያ ካርታ ውስጥ ለመኖራቸው ምንም ዓይነት ማስረጃ የማይገኝላቸው የኦሮሞ ጎሣ ሕዝቦች ወደ ዛሬይቷ ኢትዮጵያ መሀል ምድር ወረራ በሚመስል የሕዝባዊ ፍልሠት ዘመቻ በማካሄድ ከነባሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተቀላቅለዋል። ሂደቱ እጅግ ብዙ ዋጋዎችን ያስከፈለ ቢሆንም በመጨረሻ ግን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ውህደትን የፈጠሩ የኦሮሞ ጎሣ ሕዝቦች ያለ ጥርጥር የኢትዮጵያዊ ሀገረ መንግሥት ምሥረታው አካል በመሆን በኢትዮጵያዊ ውህደትና አገረመንግሥት ግንባታውም ከፍተኛ ድርሻቸውን አበርክተዋል። የታላቁ ምሑር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “የአባ ባሕርይ ድርሰቶች – ኦሮሞችን ከሚመለከቱ ሌሎች ሰነዶች ጋር” በሚባለው መፅሃፋቸው በገፅ 167 ላይ የሚከተለው ተቀምጧል። “በ16ኛው ምዕተ ዓመት ኢትዮጵያን የወረሩ ኦሮሞዎችና ሊከለክሏቸው የሞከሩ የቀድሞዎቹ ነባሮች ሁሉም ከሞላ ጎደል እኩል አያቶቻችን ሆነዋል። እኛም እንደዚያው ከሞላ ጎደል እኩል ልጆቻቸው ነን። “ ይህ አባባል ቢያንስ ሁሉንም የሚያስማማ ሃሳብ ይመስላል።

በመጨረሻም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በመዋሃዱ ክስተት ሳይጠቀስ የማይታለፈው ሕዝባዊ ፍልሠት የራስ ተፈሪያኖቹ ጥቁር ሕዝቦች ነው። ዛሬ ምናልባት የመጨረሻ በሚባል ከነባሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ፍልሠትና ውህደትን ለማካሄድ እርምጃ የወሠዱ ህዝቦች ቢኖሩ የጃማይካ፣ ካሪቢያንና ሌሎች ጥቁር አፍሪካዊያን በሻሸመኔና አካባቢዋ የሠፈሩ ኢትዮጵያዊነትን የተቀላቀሉ ሕዝቦች ናቸው። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ፈቃድና ትዕዛዝ በኢትዮጵያ የቦታና ዜግነት ስጦታን የተቀበሉት እነዚህ የዘመናችን የመጨረሻዎቹ የራስ ተፈሪ ዕምነት ተከታዮች የወደ ኢትዮጵያዊነት ፍልሠትና ውህደት ስኬታማ ህይወት መምራት መቻላቸውን ግን አንባቢያን እንዲፈርዱ ተጋብዘዋል ። በድምሩ ግን፣ ጥንታዊ የሆነው የእነዚህና ሌሎች መጤ፣ ነባርና ውህድ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ የሚለውን ጥንታዊ የወል መጠሪያ ስም ተጋርተው በትውልድ ቅብብሎሽ የኑብያ፣ የድዓማትና የአክሱም የሥልጣኔ ዘመን በመባል ታውቀል። የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሥሪት የሚቀዳውም ከእነዚህ ሁሉ የሕዝቦች ውህደትና ውጤት ነው።ተወደደም ተጠላ፣ ባለረጂም ዕድሜው ትርክትና ትውፊቱ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ሥነ መንግሥት ምሥረታ ሂደቱ ውስጥ የሰሎሞናዊና የዛጔዌ ሥርወመንግሥታት የተባሉት ዋነኞቹ መሪዎች ነበሩ። ይህም የነገሥታት ሥርዓተ መንግሥት አካሄድ እጅግ ጥንታዊ የሚባል ጊዜውን ያዋጀ የአገረመንግሥት ግንባታ ይዞታና አካል በመሆኑ ዛሬም ቢሆን ታሪካዊ ትርጉም ሰጪነቱ ግዙፍ ነው። ኢትዮጵያዊ ማንነትና ስያሜን ይዞ፣ የራስ አድርጎ ለዛሬው የግንባታ ሂደት ዘመን መድረስ የጥቁር ሕዝቦች ኩራትና ደስታ ምንጭ ነው። ለዛሬው ትውልድ፣ አድዋም የዚህ ኩራትና ደስታ አንዱ ማሳያ ምሳሌ ነው። ውስጣዊ አንድነትና ፍትሃዊ ዕኩልነት የሰፈነባት በነገሥታቱ አገራዊ የግዛት ይዞታ ስሜትና ፍላጎት ልክ የሚወዳደር እርስበእርሱ ወደከፍታ ለመውጣት መስራት የምትችል አዲስ ኢትዮጵያን መፍጠር ግን የአሁኑ ትውልድ ድርሻ ይሆናል። ዛሬ የሚታየው ስጋት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ስምና ግንባታ ሂደት የመሰናከል አደጋ ነው።
እንግዲህ የዛሬይቷ ኢትዮጵያ ለዛሬ ማንነቷና ቁመናዋ የበቃችው አያሌ የባዕድ አገራትና የአገር ውስጥ ፈተናዎችን በማለፍ እንደማንኛውም የዓለም አገራት፣ ሲመቻት በግዛትና ኃይሏ እየተስፋፋች፣ ሳይመቻት እየጠበበች ነበር። በፖለቲካና በኤኮኖሚ ኃይል የበላይነትን ሁሌም ለመያዝ አገራትና ቡድኖች የሚያደርጉት ትግል የማያቋርጥና ተፈጥሮአዊ የሚመስል የሰው ልጆች ታሪክ ነው። በዚህ መሃል መልካምድራዊ አቀማመጧም ቢሆን የራሱ ጥቅምና ጉዳትን በየጊዜው ለሕዝቧ ይዞ መገኘቱን ማስተዋል ያስፈልጋል። የክርስትና እና እስልምና ሃይማኖት የተስፋፊነት ባህርይ፣ የግዛት ሥልጣንና የመሬት ይዞታ ሃብትን በበላይነት ለመያዝ በዘመናት መካከል የተደረገው የአገር ውስጥ ተገዳዳሪ አካላት ትግልም ያልተቋረጠ ነበር።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ግን የዛሬይቷ ኢትዮጵያ አራት ዋና ዋና ተግዳሮቶች፣ ሲከፋም ጠላቶች ይታዩባታል። ሁሉም ሕዝቦቿ በእኩል ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ በበቂ ጤና እና ደስተኛነት ዜጋ ሁሉ ፍላጎቱ መሰረት የሚኖርባት አገር እንዳትሆን የሚያግዷት በአራት ዋና ተግዳሮቶች ወይም ጠላቶቿ ምክንያት ነው ብሎ ይህ መድረክ በጥብቅ ያምናል። እነዚህም አራት ዋና ጠላቶቿ፤ 1ኛ) ድህነት፣ 2ኛ) በዜጋ ደረጃ፣ እውነትንና የሳይንሳዊ ዕውቀትን መሠረት ያላደረገ ዕለታዊ መርህና ትኩረት፣ 3ኛ) ጠንካራ አንድ ሃገራዊ አንድነትንና በፍትሐዊ እኩልነት ላይ ትኩረት ያደረገ ዕውነተኛ ዕድገትን መሠረት ከሚያደረግ አገራዊና ሕዝባዊ የአደረጃጀት መርህ ይልቅ፣ በጠባብና ኋላ ቀር የጎሣ ብሔርተኝነት ላይ ተመሥርቶ የነገሠው ቡድናዊ የፖለቲካ ሥልጣንን የተጠማ የከፋፍለህ ግዛው የጥቂቶች ጥቅምን ብቻ አስከባሪ ዕሳቤና መርህ 4ኛ) የባዕድ አገራትን ብሔራዊ ጥቅም ተቃርኖና ተፅዕኖ በጥበብ ይዞ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ ጥቅም ጋር በብልሃት አግባብቶ የማስተዳደር ብቃት ያለመኖር ወይም ዕሳቤዎች ናቸው።

ለመነሻ በአጭሩ መፍትሄውም እንደሚከተለው ነው ተብሎ ይታመናል። ድህነትን መዋጋትና ማሸነፍ የሚቻለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠንካራና ታታሪ ሠራተኛነትና ምርታማነትን በዘለቄታው በማስቀጠል ነው። በመጀመሪያ የምግብ ዋስትናን በመላው አገሪቱ የሚያረጋግጥ ሥራ መሥራትን ይጠይቃል። በምግብ አቅርቦት ራስን መቻል እንደ ግለሰብም ሆነ እንደአገር ክብርና ህልውናን ያረጋግጣል። ምርትና ምርታማነት በመላው ኢትዮጵያ ለሕዝቦቿ በእኩል ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የዘመኑን የቴክኖሎጂ ማምረቻ ተቋማትን በሠፊው መገንባት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ይህም ሌላውን ግዙፉ የሥራ አጥነት ቀውስ ለመቅረፍም በቀጥታ ይረዳል። በምግብ ዋስትና ያልተቋረጠ ቀውስ ምክንያት የዛሬይቷ ኢትዮጵያ በምጣኔ ሃብት ደረጃ ከዓለማችን የድሃ ድሃ ተብላ የምትመደብ አገር ነች። ለዚህ አጭር ማሳያውም ሕዝቦቿ በዓለም ቋሚ የምግብ ተረጂ አገር መሆኗ ነው። ቀጥሎም ሥራ አጥነትና የመልካም አስተዳደር አለመኖር ተጨማሪ ማሳያዎች ናቸው። እንደ ንፁህ ውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል ችግሮችና ሌሎች እንደ መኖሪያ ቤትና የትራንስፖርት አገልግሎት ችግሮች ሁሉ የመሠረታዊ ፍላጎቶች ተደራሽነት ችግሮች ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያን ድህነት መለኪያዎች ናቸው። ስለዚህም ይህ እጅግ ከፍተኛ አገራዊ ትኩረትና የቅድሚያ ቅድሚያ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው።

ቀጥሎም አገራዊ የሥነ ባህርይና ሥነምግባር ምርመራና አዲስ ባህላዊ እድሳት ላይ አቋም በመውሰድ ዕውነትንና ሃቀኛ ባህርይን ብቻ መላበስም ዜጋዊ ግዴታ ሊሆን ይገባል። ዕውነትን ሁሌም በመናገር መኖር፣ ለህሊና መገዛት፣ ተጠያቂነትንና ፈርሃ እግዚአብሔርን በፅናት ይዞ መኖር ዛሬውኑ አስፈላጊ ነው። ዕውነትን ብቻ በመናገርና በሀቀኝነት መኖርን መመረጥ ዜጋዊ ግዴታ መሆኑ እጅግ ወሳኝነት አለው። ከዚህ በተያያዘም፣ ከፍተኛና የማይቋረጥ የሳይንሳዊ ዕውቀትና ዕድገት ትኩረት፣ እንዲሁም ለሁሉም ዜጎች እኩል ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ የአስተሳሰብ መንገድን መከተል ነው። በማንኛውም ዕለታዊ ህይወት ውስጥ ሀቀኝነት እንዲሁም ሳይንሳዊ ዕውቀትና ጥበብ በመርህ ደረጃ ሕዝባዊ መመሪያ ሊሆኑም ይገባል። ዛሬ ከምድር በታችም ሆነ ከምድር በላይ ያሉ የሃብት መፍጠሪያ የዓለማችን የሃብትና ሃይል ምንጮች እያደረቁና አሻሚነታቸው እየተጧጧፈ ከመጣ ቆይቷል። ስለዚህ በአገራት መካከል ያለውን ሽሚያ ተወዳድሮ የሃብትና ሃይል ምንጮቹን ተጠቃሚ ለመሆን ኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ መሠረት መጣል ከመቸውም ጊዜ በበለጠ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ምክንያቱም በጎሣና በጠባብ ብሔርተኝነት ተበጣጥሳ የተገኘች አገር እንኳን በዓለም አቀፍ መድረክ በዕውቀትና ሃብት በዓለም አቀፍ ብቃት ደረጃው ተገዳዳሪ የተጠቃሚነት አቅም ሊኖራት ይቅርና ራስን በምግብ የመቻል አቅሟ ጨርሶ የሚጠፋ ይሆናል። ኢትዮጵያውያን ያላቸውን የተፈጥሮና ቅርሳዊ ሃብት በዳበረ ሳይንሳዊ ዕውቀት በርብርብ መዋጮ ለዓለም አቀፉ መድረክ ተገዳዳሪ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ያነሰ ግን፣ ያለፉት 32 ዓመታቱ የጎሳ ብሔርተኝነት መርህ እንዳስከተለው አገራዊ ቀውስና ጥፋት ሁሉ ለቀጣይ የውድቀት ጉዞ የሚዳርግ ነው። የዘመኑን በቴክኖሎጂ የዳበረ የማምረቻ ተቋማትና መሣሪያዎችን በላቀ ስፋት መጠቀም መጀመር የሚቻለው፣ ሕዝቡ በዕለታዊ ዕውነተኛነትና የሳይንሳዊ ዕውቀትን መንገድ የሙጥኝ ማለትን ሲችል ነው። በመጨረሻም፣ የባዕድ አገራትን ብሔራዊ ጥቅም ከኢትዮጵያ ህዝብ ብሔራዊ ጥቅም ጋር ተቃርኖን አለዝቦና በጥበብ አዛምዶ ይዞ መኖርን መምረጥ እንደማንኛውም ብልህ አገር ተመራጭ መርህ ሊሆን ይገባል። ይህ በከፍተኛ ጥንቃቄና አርቆ አስተዋይነት ቢታሰብበት አዋጭ ምልከታ ነው። ኢትዮጵያን ካለ ባዕድ አገር ጠላት ማኖር ይቻላል ብሎ መሥራት ያስፈልጋልና። ይህ የመድረካችን እይታ በአጭሩ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ውድቀትና ስኬት ምክንያቶች ከሆኑት ግምቶች ውስጥ ዋኖቹን በአጠቃላይ አገናዝቦ የያዘ የዚህ መድረክ እይታ ነው።

እንደ ተጨማሪ መፍትሔም፣ ጥንታዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ለዛሬው ትውልድ እጅግ አስፈላጊና አይተኬ የኢትዮጵያዊ ዜግነት ሥነልቦና እና የአዕምሮ ጥንካሬ ምንጭ ነው። ተዘጋጅቶ የተቀመጠውን ጥንታዊ የታሪክ ማንነት እንዳለ በዕድለኝነት ተቀብሎ ሊጠቀመበት ያልቻለ ትውልድ ተጎጂ እንጂ ተጠቃሚ አይሆንም። የአገር ውስጥ የመንግሥታዊ ሥልጣን ጥመኛ ዓላማ ይዘው የሚገኙ ሁሉ የሕዝብ ሰላምና ዕድገት እንዳይመጣ ዕንቅፋቶች ናቸው። እንዲሁም በባዕድ አገር የኢትዮጵያ ጠላቶች ምክንያት የዛሬው ትውልድ ሙሉ መብቱ ተነፍጎና ነፃነቱ ተረግጦ ቢገኝ ሊታዘንለት የሚገባም ትውልድ አይሆንም። ይህ መድረክ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ መልካም ታሪክ ወይም ትርክት ከሀብትና ወታደራዊ ኃይል ይልቅ እጅግ የላቀና ረጂም ዕድሜ ያለው የአገራዊ አንድነት ኃይል ምንጭ ነው ብሎ በፅናት ያምናል። በተቃራኒው መጥፎና መሠሪ የሃሰት ታሪክም እንደ ትርክት እጅግ አደገኛ ጥፋትን የሚስከትል እንደሆነም ያምናል። ስለሆነም ዛሬ ተወደደም ሆነ ተጠላ፣ የሶስት ሺህ ዓመታት የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ምሥረታ ሂደትን መልካም ታሪክ ወይም ትርክት የኔ ያለው የሰለሞናዊው ሥርወመንግሥት አካል፣ የንግሥተ ሳባና ንጉሥ ሰለሞንን ትርክት እንደመነሻ መልካም ትርክቱ አድርጎ የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱ ታሪክ አካል አድርጎታል። ይህ በጊዜ ሂደት የተፈተነ ነገሥታት መራሹ ኢትዮጵያዊ የአገረመንግሥት ግንባታ ለዛሬው ትውልድ ልዩ የሥነ ልቦና ጥንካሬ ልዩ ጥቅም አለው። በእርግጥም የመጨረሻው የሶስት ሺህ ዓመታት የኢትዮጵያና ሥነመንግሥታቷ ታሪክ በዓለማችን እጅግ አስደማሚ ከሚባሉ ትርክቶች ውስጥ አንዱ ሆኖ ተቀምጧል። ይህ ቀዳማዊ ሚኒሊክን አሃዱ ንጉሥ ያደረገው የንግሥተ ሳባና ንጉሥ ሰለሞን የሥነመንግሥት ትርክት እንደመነሻ ዕውነተኛም ሆነ አፈታሪክ፣ በልዩ ሁኔታ ኢትዮጵያዊ አገረመንግሥትን በአዲስ ታሪካዊ መልክ ከመገንባት አንፃር እጅግ ጠንካራ ጠቃሚነቱ ግልፅ ሆኖአል። ከፍትሃዊ እኩልነትና ተጠቃሚነት አኳያ እንከን የለሽ ሥነመንግሥት ባይሆንም በአፍሪካ ቀንድ እንደአገር ልዩ ክብርና ዕውቅናን በዓለም ዙሪያ ያተረፈች አገር እንድትፈጠር አድርጓል። ይህም ትርክት ይባል ዕውነታ በፅሁፍ ከተቀመጠና ለዘላቂና ጠንካራ ሀገረመንግሥት ግንባታ ጥቅም ላይ ከዋለ በእርግጠኝነት ከ700 ዓመታት (በአክሱም በ1314 የወጣው ክብረ ነገሥት በተባለው መጽሃፍ ታሪክ) በላይ ዕድሜን አስቆጥሯል። ይህም በጊዜ ሂደት የተፈተነ የኃይል ምንጭነቱን በተግባር አረጋግጧል። ይህ ታሪክ ከሌሎች የኢትዮጵያ ታሪኮች ጋር ተደምሮ በጊዜ መስመር ላይ እንደሚከተለው ተቀምጧል።

 PAGE 1 – END 

Comments are closed.