Page 19

ክፍል 1፥ የመጀመሪያዎቹ አንድ ሺ ዓመታት 

1013 BC ከክርስቶስ ልደት አስቀድሞ በኢትዮጵያ ከነገሡት ነገሥታት ሁሉ ንግሥተ ሳባ እጅግ ስመ ጥሩ ነበረች።…. ይኸውም እርሷ በዚያ ዘመን ከዓረብ አገር የመን የሚባለውን ጨምራ ትገዛ ነበር።…. ግዛትዋም እጅግ ሰፊ ነበር። በስተምሥራቅ እስከማዳጋስካር በስተሰሜንና በስተ ምዕራብ እስከ ምስርና (ግብፅና) እስከ ኖብ (ኑብያ) ዳርቻ፣ በስተደቡብ ዛሬ የቪክቶሪያ ባሕር እስከ ተባለው እስከ ኒያንዛ ከሚባለውም ባሕር ነጭ ዓባይ ወጥቶ ከጣና ከሚወጣው ከጥቁር ዓባይ ጋራ በካርቱም ላይ ተገናኝቶ የሱዳንንና የምስር አገሮች ያጠጣል።    *1፣ ኅሩይ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፣ 1927  

በንግሥት ሳባም ዘመን የዳዊት ልጅ ሰለሞን በኢየሩሳሌም ንግሦ ነበር። በዚያንም ዘመን ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም የሚመላለስ ታምሪን የሚባል ነጋዴ ነበርና እርሱ በኢየሩሳሌም ያየውን የሰለሞንን ሥራ ሁሉ ስለነገራት በጆሮ ከመስማት በዓይን ማየት ይበልጣል ብላ ከአክሱም ተነስታ ወደ ኢየሩሳሌም ወረደች ። *3፣ ኅሩይ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፣ 1927 

የኤርትራንም ባሕር ተሻግራ (ወደ ሃገሯ ተመልሳ) በሐማሴን አውራጃ ማይበላ በሚባል አገር ስትደርስ ወንድ ልጅ ወለደች ። ስሙንም ኢብነ መለክ ብላ አወጣችለት። ትርጉሜውም የንጉሥ ልጅ ማለት ነው። በዘመን ብዛት ግን ንግግሩ እየተለዋወጠ ምኒሊክ ተባለ። የዚህም ትርጓሜ  ብልህ ልጅ ማለት ነው። *4፣ ኅሩይ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፣ 1927 

 

በመለኮታዊ ትርጉሙ፣ ስጦታነቱና ድንቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ተብሎ በአይሁዳውያን በልዩ ስሜት ከሚታሰበው ንብረት አንዱ የሙሴ ፅላት (ታቦት)ነው። በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊ አይሁዶች (ቤተ እስራዔላውያን) እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ንብረቱ ወደ ኢትዮጵያ የንጉሥ ሠለሞን እና ንግሥተ ሳባ ልጅ የሆነው በቀዳማዊ ሚኒሊክ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶአል ተብሎ ይታመናል። ይህ ታሪካዊ ዕምነት አወዛጋቢና ለማረጋገጥ እጅግ ፈታኝ ጥያቄ ሆኖ እስከዛሬ በዓለማችን ይገኛል።  በአክሱም በ1314 የወጣው ክብረ ነገሥት የተባለው መጽሃፍ ታሪኩን በዕውነትነት ዘግቦ አስቀምጦታል። የፅላቱን አመጣጥና በአሁኑ ዘመን የተቀመጠበትን ሥፍራ ብዙ የተለያዩ ዕምነቶችና ትንታኔዎች እንዳሉ አንባቢያን ሊያስተውሉ ይገባል። ስለዚህም በዚህ መድረክ የተቀመጡት ስለፅላቱ ትክክለኛውን አሁናዊ ዕውነታ ለማረጋገጥ ሳይሆን ከብዙዎቹ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል እንዲታወቅ ይሁን።           

987 BC ሚኒሊክ ከአባቱ ጉብኝት በኋላ ወደ ሃገሩ ኢትዮጵያ ምድር ለመመለስ ሲነሳ፣ ንጉሥ ሠለሞን በሥሩ ከአሉት የገዢ መደብ ከነበሩት ከልጆቻቸው የመጀመሪያዎችን ወጣቶች ስብስብ ፈጥሮ በእንደራሴነት ከሚኒሊክ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ሂደው የእስራዔል መንግሥትን በኢትዮጵያ ወክለው ሚኒሊክን በማገዝ በአስተዳደር እንዲመሩ አዘዘ። ከእነዚህ የሚኒሊክ አጃቢ ወጣቶች ዋናው አዛሪያህ የሚባል የእስራዔላውያኑ መንግሥት ከፍተኛ ካህን የመጀመሪያ ልጁ ነበር። አዛሪያህ የንጉሥ ሠለሞን ን ትዕዛዙን ቢጠላውም መታዘዝ ነበረበት። ስለሆነም በቁጭትና ብቀላ በሚመስል መልኩ ፅላቱን ደብቆ በመስረቅ ሚኒልክ ግማሽ መንገድ እስኪደርስ ሳያሳውቅ ወደ ኢትዮጵያ ይዞት መጣ። 2, Bernard Leeman, The Ark of the Covenant, 2011 

982 BC ንግሥተ ሳባ ልጇ ሚኒሊክ ከአባቱ በብዙ አይሁዳውያን ታጀቦ እንደተመለሰላት ባየች ጊዜ ከልጇ ጋር በዕኩል ሥልጣን ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ተስማማች።  በተለይም በግዛቷ የሚኖሩትን ቅይጡን የሳባውያን፣ የኢትዮጵያውያንና እስራዔላውያን ሕዝቦችን ሚኒልክ ሙሉ ለሙሉ እንዲያስተዳድር ተወችለት። በዚህም መንግሥታዊ ሃይማኖቱ እስራዔላዊ ወይም አይሁዳዊ ሆነ። ድንቅ ፅላቱና (ታቦቱና) የሙሴ ህግ (የኦሪት ህግ) ማዕከላዊ የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ  ሃይማኖትም ለመሆን በቃ።  መንግሥቱም እንደ አዲስ የፅዮን ሥርወ መንግሥት ወኪልና በሳባ-ሚኒሊክ የተስፋፋ ግዛት ተቆጥሮ ጅማሮው ተቀመጠ። 3, Bernard Leeman, The Ark of the Covenant, 2011. 

እናቲቱም አብረውት በአንድ ላይ ለመጡት እስራዔላውያን ጥሩ ቦታ መርጠው እንዲቀመጡ አደረገች። ሃዶራውያን የሚበዙበት የሴም ልጅ የዮቅጣን ልጆች ናቸው። የዮቅጣን ልጆች ኤል፣ ሞዳድ፣ ሣሌፍ፣ ሃስረሞት፣ ሳባ፣ አፌር፣ ኤላውጥ፣ ዩባብ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ለዮቅጣን ተወልደውለት የዘራቸው ዘሮች በሰፋርና በማሴ መካከል ይኖሩ ነበር። እንደ አረቡ ከማሼ፣ እንደ ግእዙ ሃማሴ ወይም ማሴ ከሚባል ሃገር ተነስተው ስለመጡ የሰፈሩበትን ቦታ ሃማሴን አሉት። ገዛ የሚባል የጋዛ ሰው አለቃቸውና መሪያቸው ስለነበር ስማቸው አግአዚያን እንዲባል እብነልመለክ አዘዘ። እናቱንም ማክዳ አላት። ….አግአዚያን ማለት በግእዝ፣ ገዢዎች ነፃ አውጭዎች ማለት ነው። …. ስለዚህ የሴም ልጅ የዮቅጣን ነገዶች ቋንቋቸው ግእዝ ተባለ። ልሣነ ግእዝ ብሄረ እግዚ ወንሃነ አግአዝያን ይላል።  44-45፣ የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ፣ መራሪስ፣ 1985 

ንግሥተ ነገሥት ኢትያ ልጅዋን እብነልመለክን በግዮን ወንዝ ዳርቻ እንደ አባቶቹ ህግ ወርዶ እንዲነግሥ ብትጠይቀው እንደ አባቱ እንደሰለሞን  እንደወገኖቼ እንደ እስራኤል ህግ እንጂ እንደ አንቺ ዘመዶች ሥርዓትና ህግ በወንዝ ዳር ሄጄ ሥርዓተ ንግሥን አልፈፅምም ብሎ በካህኑ ሣዶቅ ልጅ በአዛርያስ እጅ ቅባእ መንግሥት ተቀብቶ እናቱ ስትገዛው የነበረውን ከኪት እስከ ማድጋ፣ ከሱማ እስከ ላእላይ ግብፅ በአሉት ነገሥታት ላይ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብሎ ነገሠ። ስመ መንግሥቱም ምንይልክ ተባለ። አብረው ስለመጡና ስለ አገለገሉት ህዝቡን እንደ አረብ አበሺ፣ እንደግዕዝ አቡስ። ወታደሩ አግአዚኤልተብሎ የሚጠራውን አምላክ እግዚአብሔር ብሎ አዲስ ስም አወጣ። አግአዚያን ማለት በግእዝ፣ ገዢዎች ነፃ አውጪዎች ማለት ነው።  45፣ የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ፣ መራሪስ፣ 1985 

 

ከሚኒሊክ ዘመን አስቀድሞ የነበሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕገ ኦሪትን ተቀብለው ዕውነተኛውን አምላክ እስቲያመልኩ ድረስ በፀሓይና በጨረቃ በክዋክብትም በእንስሳትና በአራዊትም በዛርና በክፉ መናፍስትም ያመልኩ ነበር እንጂ ፣ እንደ ሌሎች አሕዛብ እንጨት ጠርበው ደንጊያ አለዝበው ጣዖት ቀርፀው ወይም ወርቅና ብር አፍስሰው ምስል መስለው አያመልኩም ነበር። ቀዳማዊ ሚኒሊክ ወርዶ የኦሪትን ካህናት ይዞላቸው ከመጣ በኋላ ግን እየተማሩ በእውነትኛው አምላክ ብቻ አምነው ይኖሩ ነበር።    *14፣ ኅሩይ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፣ 1927 

Comments are closed.