ክፍል 1፥ የመጀመሪያዎቹ አንድ ሺ ዓመታት
መቅድም
ዛሬ በአንድ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ስም የረጋው ያገራችንና የሕዝቡ ስም ቀድሞ ብዙ ነበር። በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ ፪ ቁጥር ፩፫፣ በዚሁ መፅሃፍ ምዕራፍ ፲ ከቁጥር ፩ እስከ ፴፪ ያለው ጽሁፍ፣ የኖህ ልጆች ሴም፣ ካም፣ ያፌት መሆናቸውን፣ የካም ልጆች ኩሽ (ኩስ፣ ቁስ)፣ ሚስራይ፣ ፋጥ፣ ከነዓን መሆናቸውን እንደሚገልፀው፣ የኩሽም ዘር በእስያ ደቡብ ከዚያም ወደ አፍሪካ ተሻግረው ተራብተው በርክተው ከዛሬው ሱዳን ዠምሮ እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ ያለውን አገር ይዘው ይኖሩ ነበር።ስለዚህ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ፫ሺና በ፩ሺ ዓመት መካከል ሁሉ ግብፆች በሐውልታቸውና በብራና (ፓፒሩስ) ጽሁፋቸው (ሂዬሮግሊፍ) ላይ እንደተውት በሰፊው ኢትዮጵያን ብዙ ጊዜ የኩሽ አገር፣ አንዳንድ ጊዜ የደቡብ ምድር፣ ወይም የነሕሴ አገር፣ አንዳንድ ጊዜ የፑንት አገር እያሉ ይጠሩት ነበር። *11፣ተክለፃድቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ኑብያ፡አክሱም፡ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት፣ 1951
በኋለኛው ዘመን ደግሞ፣ የሴም ዘሮች ነገደ ሳባና ነገደ ዮቅጣን ከደቡብ ዓረብ የኤርትራን ባሕር እየተሻገሩ፣ ከካምና ከኩሽ ዘር ጋር ተደባልቀው፣ ወይም በጦር አሸንፈው አብረው በተቀመጡ ጊዜ በስም ላይ ስም እየበረከተ ሄደ። የቀድሞዎቹ በኑብያ መንግሥታቸውን አስፍተው ኢትዮጵያ የኩሽ አገር እየተባሉ ሲቀመጡ በሥልጣኔ፣ በጽሑፍ፣ በቋንቋ የግብፅን ሲከተሉ፤ በኋላ የመጡት ደግሞ በትግሬና በሐማሴን፣ እንደዚሁም በዙሪያው ከተማቸውን እየከተሙ ከደቡብ ዓረብ ይዘውት የመጡትን ከአሶር፣ ከከለዳውያን፣ ከፊንቄ የመነጨውን የሳባ ቋንቋና ፊደል ለዛሬ ፊደላችን፣ ቋንቋና አባት የሆነውን ከሥልጣኔያቸውና ከልማዳቸው ጋር ይዘው ተቀመጡ። *12-13፣ተክለፃድቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ኑብያ፡አክሱም፡ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት፣ 1951
እንግዲህ የኩሹ ሳባ ከምሥራቅ መጥቶም ሆነ፣ ወይም ግማሹ የርሱና ያባቱ የካም ወገኖች ተደባልቀው ባሁኒቱ ኢትዮጵያና በቀድሞይቱ ኢትዮጵያ፣ በኑብያ፣ ሲኖሩ በኑብያ ያሉት ብዙውን ዘመን በነፃነት ከኖሩ በኋላ በመጨረሻ በሺ አምስት መቶ ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት ላይ በግብፅ ተገዙ። በመጨረሻ ደግሞ በሰባተኛው መቶ ዓመት ላይ እነዚሁ በግብፅ የተገዙት ኢትዮጵያውያን መልሰው ግብፅን ገዙ። በዚህን ጊዜ ሁሉ ባሁኒቱ ኢትዮጵያ የሚገኙት አግዓዚ ወይም ኃበሳን የሚባሉት ሲመቻቸው በነፃነት፣ ሳይመቻቸው ግብፅ በፊት ናፓታ በኋላ በየጊዜው እየወረሯቸውና እየገበሩ፣ በመካከላቸው ኃይለኛ ሲነሣ እየጠቀለላቸው ሲጠፉም፣ በየነገዳቸው እየተከፋፈሉ ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ መቶ ቢበዛ ሁለት መቶ ዓመት ድረስ ኖሩ። በኋላ ግን፣ በግብፅና በኑብያ የአሶር፣ የፋርስ፣ የግሪክ፣ የሮማ ገዥ እየተፈራረቀ የኑብያው የኢትዮጵያ መንግሥት ሲደክም በጎኑ ያለው የሐበሳት ወይም የአግዓዝያን ሕዝብ የአክሱምን መንግሥት እያቀና ተነሣ። *17፣ተክለፃድቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ኑብያ፡አክሱም፡ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት፣ 1951
የኑብያው ታሪክ ከግብፅ ተያይዞ፣ የአክሱም ከደቡብ ዓረብ ተዛምዶ ለአሁኑ መንግሥታችንም፣ ለሥልጣኔውም፣ ለፊደሉም፣ ለቋንቋውም፣ ለዘሩም፣ ለልማዱም ሳባና ሃበሳት የመጡበት ይኸው ደቡብ ዓረብ መሆኑ በሠፊው ይታያል። 23፣ተክለፃድቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ኑብያ፡አክሱም፡ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት፣ 1951
ነገደ ዮቅጣን መዠመሪያ በምሥራቅ ምናልባት በባቢሎን ሲኖሩ የባቢሎንን ሥልጣኔ ይዘው ወደ ደቡብ ዓረብ መጡ። በደቡብ ዓረብም ብዙ ጊዜ ከተቀመጡ በኋላ ሕንዶች ወይም ሌላ ሕዝብ እየወጉ ስለአስቸገሩዋቸው ይሁን ወይም በፈቃዳቸው ለምለም አገር ፍለጋ ይሁን፣ ከደቡብ ዓረብ ወደ ኢትዮጵያ፣ ሰሜን ተሻግረው ተቀመጡ። ከዚያም ነገደ ዮቅጣን ግማሾቹ በትግሬ፣ ግማሾቹ በአዳል፣ ግማሾቹ በውጋዴን አገር ተከፋፍለው ይኖሩ ነበር።…. የሕንድ ንጉሥ ራማ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በዚያ ዘመን የነበረውን ንጉሥ ጴኦሪን ወግቶ ኢትዮጵያን ባስገበረ ጊዜ፣ እነዚሁ ነገደ ዮቅጣን ከየአለበት ተሰብስበው ከመካከላቸው አክናሁስን አንግሠው፣ የሕንዱን ንጉሥ ራማን ተዋግተው ስለአስወጡ፣ ነገደ አጋዓዝያን (ነፃ አውጭዎች) የሚባል ስም ተሰጣቸው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ፣ ነፃ ባወጡት አገር በነገደ ካም ነገሥታት ምትክ ገብተው መንግሥታቸውን መሠረቱና የነገደ ዮቅጣን ሕዝብ ከነገደ ካም ዘር ጋር ተደባልቀው ይኖሩ ዠመር ማለት ነው። ነገር ግን በኢትዮጵያ የቆየው የካም ሕዝብ ከደቡብ ዓረብ የመጣው የዮቅጣን ሕዝብ በልማድ፣ በወግ፣ በሥርዓት፣ በአምልኮና፣ በቋንቋ መለያየታቸው የታወቀ ስለሆነ፣ ከመርዌ እስከ ኤርትራ ባሕር ባለው በሰፊው በኢትዮጵያ ምድር እየተለያዩም እየተገናኙም ኃይለኛ ሆኖ ለነገሠው እየገበሩ፣ ያም ሲጠፋ እየተለያዩ በየነገዳቸው እንደልማዳቸው መኖራቸው የታወቀ ነው። *37፣ተክለፃድቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ኑብያ፡አክሱም፡ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት፣ 1951