Page 3

ክፍል 1፥ የመጀመሪያዎቹ አንድ ሺ ዓመታት

1013 BC ከክርስቶስ ልደት አስቀድሞ በኢትዮጵያ ከነገሡት ነገሥታት ሁሉ ንግሥተ ሳባ እጅግ ስመ ጥሩ ነበረች።…. ይኸውም እርሷ በዚያ ዘመን ከዓረብ አገር የመን የሚባለውን ጨምራ ትገዛ ነበር።…. ግዛትዋም እጅግ ሰፊ ነበር። በስተምሥራቅ እስከማዳጋስካር በስተሰሜንና በስተ ምዕራብ እስከ ምስርና (ግብፅና) እስከ ኖብ (ኑብያ) ዳርቻ፣ በስተደቡብ ዛሬ የቪክቶሪያ ባሕር እስከ ተባለው እስከ ኒያንዛ ከሚባለውም ባሕር ነጭ ዓባይ ወጥቶ ከጣና ከሚወጣው ከጥቁር ዓባይ ጋራ በካርቱም ላይ ተገናኝቶ የሱዳንንና የምስር አገሮች ያጠጣል።    * 1፣ ኅሩይ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፣ 1927

በንግሥት ሳባም ዘመን የዳዊት ልጅ ሰለሞን በኢየሩሳሌም ንግሦ ነበር። በዚያንም ዘመን ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም የሚመላለስ ታምሪን የሚባል ነጋዴ ነበርና እርሱ በኢየሩሳሌም ያየውን የሰለሞንን ሥራ ሁሉ ስለነገራት በጆሮ ከመስማት በዓይን ማየት ይበልጣል ብላ ከአክሱም ተነስታ ወደ ኢየሩሳሌም ወረደች ። *3፣ ኅሩይ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፣ 1927

 

የኤርትራንም ባሕር ተሻግራ (ወደ ሃገሯ ተመልሳ) በሐማሴን አውራጃ ማይበላ በሚባል አገር ስትደርስ ወንድ ልጅ ወለደች ። ስሙንም ኢብነ መለክ ብላ አወጣችለት። ትርጉሜውም የንጉሥ ልጅ ማለት ነው። በዘመን ብዛት ግን ንግግሩ እየተለዋወጠ ምኒሊክ ተባለ። የዚህም ትርጓሜ  ብልህ ልጅ ማለት ነው። *4፣ ኅሩይ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፣ 1927

በመለኮታዊ ትርጉሙ፣ ስጦታነቱና ድንቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ተብሎ በአይሁዳውያን በልዩ ስሜት ከሚታሰበው ንብረት አንዱ የሙሴ ፅላት (ታቦት)ነው። በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊ አይሁዶች (ቤተ እስራዔላውያን) እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ንብረቱ ወደ ኢትዮጵያ የንጉሥ ሠለሞን እና ንግሥተ ሳባ ልጅ የሆነው በቀዳማዊ ሚኒሊክ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶአል ተብሎ ይታመናል። ይህ ታሪካዊ ዕምነት አወዛጋቢና ለማረጋገጥ እጅግ ፈታኝ ጥያቄ ሆኖ እስከዛሬ በዓለማችን ይገኛል።  በአክሱም በ1314 የወጣው ክብረ ነገሥት የተባለው መጽሃፍ ታሪኩን በዕውነትነት ዘግቦ አስቀምጦታል። የፅላቱን አመጣጥና በአሁኑ ዘመን የተቀመጠበትን ሥፍራ ብዙ የተለያዩ ዕምነቶችና ትንታኔዎች እንዳሉ አንባቢያን ሊያስተውሉ ይገባል። ስለዚህም በዚህ መድረክ የተቀመጡት ስለፅላቱ ትክክለኛውን አሁናዊ ዕውነታ ለማረጋገጥ ሳይሆን ከብዙዎቹ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል እንዲታወቅ ይሁን። 

987 BC ሚኒሊክ ከአባቱ ጉብኝት በኋላ ወደ ሃገሩ ኢትዮጵያ ምድር ለመመለስ ሲነሳ፣ ንጉሥ ሠለሞን በሥሩ ከአሉት የገዢ መደብ ከነበሩት ከልጆቻቸው የመጀመሪያዎችን ወጣቶች ስብስብ ፈጥሮ በእንደራሴነት ከሚኒሊክ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ሂደው የእስራዔል መንግሥትን በኢትዮጵያ ወክለው ሚኒሊክን በማገዝ በአስተዳደር እንዲመሩ አዘዘ። ከእነዚህ የሚኒሊክ አጃቢ ወጣቶች ዋናው አዛሪያህ የሚባል የእስራዔላውያኑ መንግሥት ከፍተኛ ካህን የመጀመሪያ ልጁ ነበር። አዛሪያህ የንጉሥ ሠለሞንን ትዕዛዙን ቢጠላውም መታዘዝ ነበረበት። ስለሆነም በቁጭትና ብቀላ በሚመስል መልኩ ፅላቱን ደብቆ በመስረቅ ለሚኒልክ ግማሽ መንገድ እስኪደርስ ድረስ ሳያሳውቀው ወደ ኢትዮጵያ ይዞት መጣ። 2, Bernard Leeman, The Ark of the Covenant, 2011

982 BC ንግሥተ ሳባ ልጇ ሚኒሊክ ከአባቱ በብዙ አይሁዳውያን ታጀቦ እንደተመለሰላት ባየች ጊዜ ከልጇ ጋር በዕኩል ሥልጣን ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ተስማማች።  በተለይም በግዛቷ የሚኖሩትን ቅይጡን የሳባውያን፣ የኢትዮጵያውያንና እስራዔላውያን ሕዝቦችን ሚኒልክ ሙሉ ለሙሉ እንዲያስተዳድር ተወችለት። በዚህም መንግሥታዊ ሃይማኖቱ እስራዔላዊ ወይም አይሁዳዊ ሆነ። ድንቅ ፅላቱና (ታቦቱና) የሙሴ ህግ (የኦሪት ህግ) ማዕከላዊ የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ  ሃይማኖትም ለመሆን በቃ።  መንግሥቱም እንደ አዲስ የፅዮን ሥርወ መንግሥት ወኪልና በሳባ-ሚኒሊክ የተስፋፋ ግዛት ተቆጥሮ ጅማሮው ተቀመጠ። 3, Bernard Leeman, The Ark of the Covenant, 2011.

እናቲቱም አብረውት በአንድ ላይ ለመጡት እስራዔላውያን ጥሩ ቦታ መርጠው እንዲቀመጡ አደረገች። ሃዶራውያን የሚበዙበት የሴም ልጅ የዮቅጣን ልጆች ናቸው። የዮቅጣን ልጆች ኤል፣ ሞዳድ፣ ሣሌፍ፣ ሃስረሞት፣ ሳባ፣ አፌር፣ ኤላውጥ፣ ዩባብ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ለዮቅጣን ተወልደውለት የዘራቸው ዘሮች በሰፋርና በማሴ መካከል ይኖሩ ነበር። እንደ አረቡ ከማሼ፣ እንደ ግእዙ ሃማሴ ወይም ማሴ ከሚባል ሃገር ተነስተው ስለመጡ የሰፈሩበትን ቦታ ሃማሴን አሉት። ገዛ የሚባል የጋዛ ሰው አለቃቸውና መሪያቸው ስለነበር ስማቸው አግአዚያን እንዲባል እብነልመለክ አዘዘ። እናቱንም ማክዳ አላት። ….አግአዚያን ማለት በግእዝ፣ ገዢዎች ነፃ አውጭዎች ማለት ነው። …. ስለዚህ የሴም ልጅ የዮቅጣን ነገዶች ቋንቋቸው ግእዝ ተባለ። ልሣነ ግእዝ ብሄረ እግዚ ወንሃነ አግአዝያን ይላል።  44-45፣ የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ፣ መራሪስ፣ 1985

ንግሥተ ነገሥት ኢትያ ልጅዋን እብነልመለክን በግዮን ወንዝ ዳርቻ እንደ አባቶቹ ህግ ወርዶ እንዲነግሥ ብትጠይቀው እንደ አባቱ እንደሰለሞን  እንደወገኖቼ እንደ እስራኤል ህግ እንጂ እንደ አንቺ ዘመዶች ሥርዓትና ህግ በወንዝ ዳር ሄጄ ሥርዓተ ንግሥን አልፈፅምም ብሎ በካህኑ ሣዶቅ ልጅ በአዛርያስ እጅ ቅባእ መንግሥት ተቀብቶ እናቱ ስትገዛው የነበረውን ከኪት እስከ ማድጋ፣ ከሱማ እስከ ላእላይ ግብፅ በአሉት ነገሥታት ላይ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብሎ ነገሠ። ስመ መንግሥቱም ምንይልክ ተባለ። አብረው ስለመጡና ስለ አገለገሉት ህዝቡን እንደ አረብ አበሺ፣ እንደግዕዝ አቡስ። ወታደሩ አግአዚኤል ተብሎ የሚጠራውን አምላክ እግዚአብሔር ብሎ አዲስ ስም አወጣ። 45፣ የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ፣ መራሪስ፣ 1985

ከሚኒሊክ ዘመን አስቀድሞ የነበሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕገ ኦሪትን ተቀብለው ዕውነተኛውን አምላክ እስቲያመልኩ ድረስ በፀሓይና በጨረቃ በክዋክብትም በእንስሳትና በአራዊትም በዛርና በክፉ መናፍስትም ያመልኩ ነበር እንጂ ፣ እንደ ሌሎች አሕዛብ እንጨት ጠርበው ደንጊያ አለዝበው ጣዖት ቀርፀው ወይም ወርቅና ብር አፍስሰው ምስል መስለው አያመልኩም ነበር። ቀዳማዊ ሚኒሊክ ወርዶ የኦሪትን ካህናት ይዞላቸው ከመጣ በኋላ ግን እየተማሩ በእውነትኛው አምላክ ብቻ አምነው ይኖሩ ነበር።    *14፣ ኅሩይ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፣ 1927

በዚህ በ፲ኛው ፣ በ፱ኛውና በ፰ኛውም መቶ ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ በኋላ የገነነውና አሁን ገናንነቱን በሐውልቱና በጽሑፉ የምናውቀው የአክሱም መንግሥት እስከአሁን አለመነሣቱን የሳባውያንና የአክሱምን ታሪክ የመረመሩት ሊቃውንት ሁሉ አረጋግጠዋል ። ከአትባራ ወንዝ ወዲያ በኑብያ ግን እነዚያው በኢትዮጵያዊነት የምንጠራቸው መጀምሪያ ነፃ ሆነው ፣ በኋላ እነቱትሞሲስ ቀጥሎም እነራምሲስ ፪ኛ ካስገበሩዋቸው ወዲህ አሁንም አንዳንድ ጊዜም እነሱ እያጠቁ ፣ አንዳንድ ጊዜም በግብፅውያኑ እየተገዙ ኑሯቸውን ይቀጥላሉ ።    *78፣ተክለፃድቅ መኩሪያ ፣ የኢትዮጵያታሪክ ፤ ኑብያ፡አክሱም ዛጉዌ እስከ ይኩኖአምላክ ዘመነመንግሥት ፣ 1951

የኩሽ ሕዝብ ፣ የሳባሕዝብ ፣ ነገደዮቅጣን ፣ ነገደአግዓዝያን ፣ ሂማሪያት ፣ ሳባውያን ፣ ሀበሳን እያለ በዝርዝር ሲጠራው ፣ ይህን ሁሉ ስም ደግሞ አቅፎ የሚገኘው ስም ኢትዮጵያ የተባለው ሥያሜ ነው ። ኢትዮጵያ ሲል በቀድሞ ዘመን ከግብፅ በደቡብ ፣ ከኤርትራ ባሕር ወደ ምዕራብ እስከ አትላንቲክ ድረስ ያለው አገር ሁሉ በሰፊው ኢትዮጵያ የተባለበት ጊዜ አለ ። ባንዳንድ ጸሐፊዎች ዘንድ ምሥራቁ ኢትዮጵያ ፣ ምዕራቡ ኢትዮጵያ ተብሎ ይገኛል ። ለናፓታ መንግሥት ብቻውን ለራሱ የኢትዮጵያነትን ስም ሰጥተውት ይገኛል ። በዚሁ ምክንያት ባለፉት ምዕራፎች እንደምናስታውሰው ግብፅን የገዙትን እነፒያንኪን ፣ እነሻባካን ፣ የቀድሞ የግሪክና የሮማ ጸሐፊ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው ብለው ለግብፅ ግዛት 25ኛ ሥርወመንግሥት አድርገዋቸዋል ።   የናፓታንና የመርዌን ሕዝብ ግብፆችና አሶሮች ኩሽ ሲሉዋቸው ፣ ግሪኮችና ሮማውያኑ በብዙ ቦታ ኢትዮጵያውያን ብለውት ይገኛል ። *182፣ተክለፃድቅ መኩሪያ ፣ የኢትዮጵያታሪክ ፤ ኑብያ፡አክሱም፡ዛጉዌ እስከ ይኩኖአምላክ ዘመነመንግሥት ፣ 1951

ከውጭ እየመጣ የሚደረበው ሁሉ የራሱን ስምና ቋንቋ ይዞ በመኖር ፈንታ አብዛኛውን ጊዜ በፈታኞቹና በነባሮቹ ተውጦ ይገኛል ። በነዋሪው በካም ሕዝብ ላይ ነገደ ዮቅጣን የተባሉትን አግዓዝያን በየዘመኑ ገብተው በገዥነትም በነዋሪነትም በኢትዮጵያ ከተመሠረቱ ወዲህ በየጊዜው በነሱ ላይ የተጨመረው ሕዝብ ከየታሪኩ ሲለቅም የእስራዔል ፣ የከነዓን ፣ የፋርስ ፣ የሕንድ ዘር በየጊዜው በየምክንያቱ እየገባ እንደተጨመረ ይታወቃል ።     *183፣ ተክለፃድቅመኩሪያ ፣ የኢትዮጵያታሪክ ፤ ኑብያ፡አክሱም፡ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት ፣ 1951

800 BC ኩሽ ከግብፅ በስተደቡብ በአሁኑ ሱዳን ውስጥ በአባይ ወንዝ ሸለቆ ይገኝ የነበረው አገር / ስርወመንግሥትና ህዝብ ስያሜ ነው ። የኩሽ ስርወመንግሥት የኑቢያ ስርወ መንግሥት በመባልም ይታወቃል ። የዚህ ስርወ መንግሥት የመጀመሪያው መቀመጫና መነሻ ከርማ ነው ። ይህ ስርወ መንግሥት በ2500 – 1567 ዓ .ዓ .ባለው ጊዜ እንደተነሳ ይገመታል ። ከ1567 – 1090 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ከርማ በግብፅ ፈርዖኖች ቅኝ ግዛት አስተዳደር ሥር ወደቀ ። በዚህ ዘመን የተፃፉ የታሪክ ምንጮች አገሩን ኩሽ ይሉታል ።…. የኩሽ ስርወ መንግሥት በስምንተኛው መቶ ክፍለዘመን በተራው ግብፆችን ወርሮ 25ኛውን ስርወ መንግሥት በማቋቋም ሰፊ ግዛት መስርቶ ግብፅን ለሶስት አራተኛ ክፍለ ዘመን ያህል አስተደድሯል ።    *74 ,ተገኘ ፣ በራራ – ቀዳሚት አዲስአበባ ፣ 2020

በሚኒሊክ የጀመረው ከአይሁዳዊው የሀገረ መንግሥት ምሥረታ ማግሥት ጀምሮ አይሁዳዊው ባህል፣ ሥልጣኔና ዕምነት ማዕከላዊነትን ይዞ በኢትዮጵያ ተቀመጠ ። የኦሪት ህግና መንግሥት በአይሁዳዊነቱ በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ነገሠ ። በኢትዮጵያ የዛሬዎቹ ቤተ እስራዔላውያን ማንነት ምንጭም ከዚህ ዘመን አይሁዳውያን ወደ ኢትዮጵያ ካደረጉት ፍልሠት ጀምሮ የሚቀዳ ነው ። አይሁዳዊ አገዛዙ ጥቂት ምዕተ ዓመታትንም እንዳስቆጠረ የድዓማት ሥልጣኔ ዘመን ማዕከላዊነቱን ተረከበ ። ምንም እንኳ የድዓማት የሥልጣኔ ዘመን ተነስቶ የከሰመበት ወቅት በውል ባይታወቅም ፣ በቀይ ባህር ዳርቻ በድንገት የተፋፋመውን ንግድ የደቡብ ዓረቢያ የንግድ ሕዝቦችን ከፍተኛ ፍልሠት አስከተሎ በሠፊው አስተናገደ ።

800 BC ከአትባራ ወዲያ ያሉት የኑብያ ኢትዮጵያውያን ከሺ ስድስት መቶ ዓመት ወዲህ በግብፆች ተገዝተው ፣ ኢትዮጵያውያንም በ800 ዓ.ዓ. ከክርስቶስ ልደት በፊት መልሰው ግብፆችን የገዙበት ጊዜ አለ ። ነገር ግን እነዚህ ግብፅን መልሰው የገዙት የኑብያ ኢትዮጵያውያን እንጂ ሳባውያንና ሃበሳን አይደሉም ። ሳባውያንና ሃበሳን ከየመን ወደ ኢትዮጵያ ሰሜን የገቡበት ጊዜ የዛሬ ሊቃውንትና መርማሪዎች ከክርስቶስ ልደት በፊት ቢበዛ ፷0 ዓመት ግድም ላይ አድርገውታል ። ከዚያ በፊት ሥልጣኔና ፊደል የሌላቸው ሳባውያን ገብተው እንደሆነ አይታወቅም ። *34፣ተክለፃድቅ መኩሪያ ፣ የኢትዮጵያታሪክ ፤ ኑብያ፡አክሱም፡ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት ፣ 1951

እንግዲህ እነዚህ ሁለት የግብፅና የኑብያ ኢትዮጵያ የጥንት መንግሥቶች ለየብቻ ንግድና ሥልጣኔ እየተለዋወጡ ሲኖሩ ፣ የአምልኮአቸውም ዓይነት ፀሃይዋን ፣ ዋርካውን ፣ ተራራውን ፣ ወንዙን (ዓባይን )፣ አሞራን በማምለክ ይመሳሰላል ። ለእነዚህም መሥዋዕትን ያቀርባል ። *35፣ተክለፃድቅ መኩሪያ ፣ የኢትዮጵያታሪክ ፤ ኑብያ፡አክሱም፡ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት 1951

Comments are closed.