Page 4 START
በፍልሠት ከተለያዩ ሥፍራዎች መጥተው የተዋሃዱት ኢትዮጵያዊ ከመሆናቸው አስቀድሞ በምድረ ኢትዮጵያ የነበሩትን ሕዝቦች፣ በሚከተለው ሰንጠረዥ የምድረ ኢትዮጵያ ነባር ሕዝብ ተብለው ታሪክ ይዘታቸው የሚከተለውን ይመስላል።
34-35፣ የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ፣ መራሪስ፣ 1985
በዚህ በ፲ኛው፣ በ፱ኛውና በ፰ኛውም መቶ ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ በኋላ የገነነውና አሁን ገናንነቱን በሐውልቱና በጽሑፉ የምናውቀው የአክሱም መንግሥት እስከአሁን አለመነሣቱን የሳባውያንና የአክሱምን ታሪክ የመረመሩት ሊቃውንት ሁሉ አረጋግጠዋል። ከአትባራ ወንዝ ወዲያ በኑብያ ግን እነዚያው በኢትዮጵያነት የምንጠራቸው መጀምሪያ ነፃ ሆነው፣ በኋላ እነቱትሞሲስ ቀጥሎም እነራምሲስ ፪ኛ ካስገበርዋቸው ወዲህ አሁንም አንዳንድ ጊዜም እነሱ እያጠቁ፣ አንዳንድ ጊዜም በግብፅውያኑ እየተገዙ ኑሯቸውን ይቀጥላሉ። *78፣ተክለፃድቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ኑብያ፡አክሱም፡ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት፣ 1951
ከድዓማት እስከ አክሱማዊ ሥረወ መንግሥቱ ተመሥርቶ ገናና ለመሆን እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ያለው ታሪክ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት በተጨባጭ ታሪካዊ የማስረጃ ቅርስ በተገቢው መጠን ባልተዘጋጀበት፣ ስለ ድዓማት ዘመን ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ታሪክ በዋና ትኩረትነት ለጊዜው ብዙ ማለት አይቻልም። ከዚህም የተነሳ በዋናነት የዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ታሪክ የፖለቲካና መንግሥታዊ ሥልጣኑን ከንግሥተ ሳባ ጀምሮ ሲረካከቡ ከመጡት ነገሥታት ስምና የሥልጣን ቆይታ ዘመናቸው ብዙም ያለፈ ሆኖ አልተገኘም። የተሻለ ቅርሳዊ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ማስረጃዎች በአሁኑ ትውልድ ሥራ እስከሚጨመርበት ጊዜ ድረስም ቢሆን ፖለቲካዊና መንግሥታዊ ሥልጣን የያዙትን የድዓማት ሥርወመንግሥት መሪዎች ስምና የሥልጣን ዘመን እናያለን። እዚህ ላይ አንባብያን የራሳቸውን ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥናታዊ ሥራዎች ምርምር ቢሠሩ ይመከራል። ለጊዜው በቂ የአርኪዮሎጂና ሌሎች ሳይንሳዊ የታሪክ ማስረጃ ምንጮች እንደሌሉም መገንዘብ ግድ ይሆናል።
የናፓታና የአክሱም አገሮች በአገር ጉርብትናም በዘርም የሚገናኙ ሁለቱ በየተራ የገነኑ ወንድማማቾች ናቸው። ሁለቱ አገሮች በመልክ፣ በቅርፅ፣ በደም ግባት፣ በአገር ካርታ አቀማመጥ በሥርዓትና በልማድ በቤትና በዕቃ፣ በጦር መሣሪያ በሙሉም ባይሆን በመጠኑ ተመሳስለው፣ ተከላልሰው ይገኛሉ። *183፣ተክለፃድቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ኑብያ፡አክሱም ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት፣ 1951
በመዠመሪያ ናፓታ፣ ቀጥሎ መርዌ በገነነበት ሰዓት በአክሱም ዙሪያ የሚገኘው አገር በነርሱ መገዛቱ፣ አክሱም በገነነ ጊዜ ደግሞ አብርሃና (ኢዛና) ተከታዮቹ ኑብያን (ናፓታና መርዌ) መግዛታቸው የታወቀ ስለሆነ ይህ የእርስ በርስ መገዛዛት አንድነታቸውን ጭምር ያስረዳል። በዚሁ የተነሣ አብዛኛው ጸሐፊ ሁሉ ይልቁንም ያገራችን ሊቃውንት ከአክሱም በፊት በናፓታና በመርዌ የነገሡትን ነገሥታት የኢትዮጵያ ነገሥታት እያደረገ ዝርዝራቸውን ከነስማቸው ከአክሱሙ ነገሥታት ጋር ተርታ እየሰጠ ይፅፋል። *184፣ተክለፃድቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ኑብያ፡አክሱም ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት፣ 1951
እንግዲህ ጥንታዊ ኢትዮጵያን እንደ አንድ ሳንቲም መስሎ መግለፁ ጥንታዊ ኢትዮጵያ አንድ አካልነትን ይዛ በሁለት የአንድ ሳንቲም ገፅታዎች የምትገለፅ አገር እንደነበረች በቀላሉ ለማሳየት ይረዳል። ከነገደ ሴም ሐረግ የሚመደበው በቀዳማዊ ሚኒሊክ አጃቢዎቹና መሪነትና ከደቡብ አረቢያ የመጡት ነገደ ዮቅጣኖች እጅግ ሠፊ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነው ከአንደኛው ጥንታዊ ምድረ ኢትዮጵያ ሲመደቡና እንደአንደኛው የሳንቲሙ ገፅታ ሲሆኑ፣ በሁለተኛው የሳንቲሙ ገፅታ ጥንታዊ ምድረ ኢትዮጵያ ደግሞ ከነገደ ካም የሚመደበው የኑብያ ኢትዮጵያ ህዝቦች ይገኙበት ነበር። በዚህ በመጀምሪያው አንድ ሺህ ዓመታቱ የጥንታዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ተቀምጦ የምናገኘው የእነዚህ የተቀላቀሉ የሁለት ነገድ መሪዎች የጥንታዊ ኢትዮጵያን መሪነት ዝርዝር ታሪክ ይሆናል። ማለትም እንደ ከርማ፣ ናፓታና መርዌ ባሉ የነገደ ኩሽ ኑብያ መናገሻዎችና እንደ የሃ፣ አዶሊስና አክሱም ባሉ መናገሻዎች ደግሞ ከሴምአውያን ነገድ የተዛመዱ የድዓማትና አሱማውያን ሥልጣኔ መሪዎች ዝርዝር ነው።
ይህ ከዚህ በታች ብዙ ዘመናትን እየዘለለ ነገሥታቱን መርጦ መጥቀስ ያስፈለገው ለምሳሌነት ማሳያ ብቻ እንዲሆን በማሰብ ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ የተዘለለው ዓመታት የራሱ መሪና በውል የታወቀ ስምና ዘመን እንዳለው ሊታወቅ ይገባል።
930 BC አሜንሆቴፕ፣ ዘግዱር የነገሡበት ዓመታት ብዛት 41
889 BC አክሱማይ ራሚሱ፣ ወረደ ፀሃይ የነገሡበት ዓመታት ብዛት 20
751 – 716 BC ፒያንኪ ፪ኛ ፣ የነገሡበት ዓመታት ብዛት 34
716 – 701 BC ሻባካ፣ የነገሡበት ዓመታት ብዛት 15
701 – 690 BC ሻባታካ፣ የነገሡበት ዓመታት ብዛት 12
690 – 664 BC ታርሐቃ፣ የነገሡበት ዓመታት ብዛት 26
664 – 656 BC ታኑታሙን፣ የነገሡበት ዓመታት ብዛት 8
594 BC ዙዋሬንብረት፣ አስፑርታ የነገሡበት ዓመታት ብዛት 41
521 BC ሶፎልያ፣ ነኪቦን የነገሡበት ዓመታት ብዛት 31
423 BC አጵራሶ፣ ታልክሃርሜን የነገሡበት ዓመታት ብዛት 10
328 BC ናስታሴን የነገሡበት ዓመታት ብዛት 10
296 BC አርካሚን ፪ኛ የነገሡበት ዓመታት ብዛት 10
233 BC ኒኮሲስ፣ ቅንዳኬ ፭ኛ የነገሡበት ዓመታት ብዛት 10
138 BC ነግሣይ፣ ብሲኒቲ የነገሡበት ዓመታት ብዛት 10
98 BC ሠናይ የነገሡበት ዓመታት ብዛት 10
77 BC ዳዊት ፪ኛ የነገሡበት ዓመታት ብዛት 10
29 BC አሞይ፣ መሐሲ የነገሡበት ዓመታት ብዛት 5
8 BC ባዚን የነገሡበት ዓመታት ብዛት 8
*74-365 ፣ተክለፃድቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ኑብያ፡አክሱም፡ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት፣ 1951
ለወደፊቱ፣ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን የጥንታዊ ኢትዮጵያ ነገሥታት አበይት የሚባሉ ታሪኮችን ወደፊት እየመጠንን በዚሁ ዓምድ ጨምረን እናብራራለን። እነዚህ ከሶስቱ የመጀመሪያው አንድሺህ ዓመታቱ ከሥርዓተ መንግሥቱ መሪዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ብቻ ተለይተው ለናሙና ዕይታ ብቻ ተመርጠው ለጊዜው የቀረቡ ናቸው። ከዚህ በላይ እንደተገለፀውም እነዚህም ሆነ ሌሎች እንደነዚህ ያልተዘረዘሩ የኢትዮጵያ ነገሥታት የኑብያና ሳባውያን የቅይጥ ኢትዮጵያ ድምር ውጤቶች መሆናቸውን ማስተዋል ያስፈልጋል። ለጊዜው በዚህ ያልተዘረዘሩትንም ሆነ ሌሎች ተዛማጅ የወቅቱን መጠነኛ ታሪካዊ ዘገባዎች ወደፊት በሂደት እዚሁ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የምናቀርብ መሆኑን እንገልፃለን።
አክሱማውያን ከሴም ወገን ከወረደው ከዮቅጣን ሳባ የመጡ ሲሆኑ የኑብያ (ናፓታና መርዌ) ሕዝብ ከካምና ኩሽ፣ ከወረዱት ሳባ የመጡ ስለሆነ በአክሱሞች ዘንድ ሴማዊ፣ በኑብያዎች ዘንድ የካምና የኩሽ ዘር ይበዛል።
*184፣ተክለፃድቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ኑብያ፡አክሱም፡ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት፣ 1951
END OF PAGE 4