Page 5

500 BC በመጀመሪያ ሙካሪብ የተሰኙት የሳባ ገዥዎች፣ መንግሥታዊና ሃይማኖታዊ ሥልጣን አጣምረው የያዙ መሪዎች ነበሩ። ኋላ በ5ኛውና በ4ኛው ዓመተ ዓለም ላይ፣ ሥልጣኑ ዓለማዊ ሆነ።  የሳባ መንግሥት በንግድ አማካይነት ወደ አፍሪካ አህጉር መስፋፋት የጀመረው በዚህን ወቅት ሳይሆን አይቀርም። እንደዚሁም ሳባውያን ነጋዴዎችና መንደር ቆርቋሪዎች ቀይ ባህርን ተሻግረው ማዶ ባለው ቀበሌ ላይ መስፈር የሚጀምሩት በዚህን ወቅት ነው። ይህ ከአረቢያ ወደ ዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጠረፍ የሚደረገው ፍልሠት ቀስ በቀስ የማያቋርጥ ንቅናቄ ሆኖ ይቀጥላል። *15, የኢትዮጵያ ታሪክ , ባርትኒስኪና ኒየችኮ   

200 BC በደቡብ ዓረቢያ በቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ፣ በዛሬዎቹ የመንና ኤደን ምድር አካባቢ፣ ዓረቢያ ፌሊክስ – “ዕድለኛዋ ዓረቢያ”- ተብሎ በሚጠራው ደቡባዊ ክፍል፣ አስደናቂ የሆኑ የከተማ መንግሥት ሥልጣኔዎች ያበቡበት ዘመን ነበር። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1ኛው መክዘ ውስጥ በዚህ አካባቢ ፣ ከፍ ካለ የኤኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ባህላዊ ብልፅግና ደረጃ ላይ የደረሱ፣ ለበላይነት እርስ በርሳቸው የሚታገሉ ማይን፣ ካታባን፣ ሳባ እና ሃድራሙት የተባሉ መንግሥታት ነበሩ። ….ሳባ ለረጂም ጊዜ የበላይነቱን ይዛ ቆይታለች። *15, የኢትዮጵያ ታሪክ , ባርትኒስኪና ኒየችኮ    

ቀስ በቀስ ግን ባለማቋረጥ የገባው የደቡብ ዓረቢያ ሕዝብ ቁጥሩ እየበዛ ሲሄድ፣ በአፍሪካው አህጉር የባህር ጠረፍ ላይ እየተሰባሰበ በመንደር መኖር ከጀመረ በኋላ ፣ ባህር ማዶ ከሚገኘው እናት አገሩ ጋር ጥብቅ የንግድ ትስስር ይመሠርታል። የአፍሪካው አህጉር በዚያን ጊዜ በጣም ተፈላጊ የነበሩ ፣ እንደ ዝሆን ጥርስ፣ ቅመማ ቅመምና የሙጫ ተክሎችን የመሳሰሉ ሸቀጦችን ላኪ ነበር።… በ ፩ኛው መቶ ዓመተ ዓለም ውስጥ፣ በትላልቅና በትናንሽ ስብስቦች እየሆኑ ፣ የዳበረ የቴክኒካዊና መንፈሳዊ ሥልጣኔአቸውን ይዘው የመጡት እነዚህ የደቡብ ዓረቢያ ሰፋሪዎች፣ በዓይነቱ ላቆጠቆጠው የኢትዮጵያ ሥልጣኔ የመሠረት ደንጊያ ጣሉ። ኢትዮጵያ ከእስልምና በፊት የነበረውን የዓረብ ዓለም ሥልጣኔ በሚወክሉት በነዚህ መሥራቾች አማካይነት ከሴማዊው ሥልጣኔ ጋር የምት ተሳሰር ሲሆን፣ ይህ ሥልጣኔ በሥፍራው ከነበረው ከኩሳ (ኩሽ) ሕዝቦች አፍሪካዊ ሥልጣኔ ጋር ተቀላቅሏል። *15, የኢትዮጵያ ታሪክ , ባርትኒስኪና ኒየችኮ   

200 BC በቀይ ባሕር ዳርቻ በዙላ ባሕረሰላጤ የሚገኘው የአዶሊስ ወደብና የዳህላክ ደሴቶች ለአክሱም ሥልጣኔ መነሳትና መፋፋም ዋና ማዕከል ነበረ። አዶሊስ ለ700 (ከ150 ዓመት ዓለም እስከ 650 ዓመት ምህረት) ዓመታት ገደማ ያህል የከፍተኛ ባህልና ንግድ መሳለጫ ወደብ ሆና በመካከለኛው ባህርና በሩቅ ምሥራቅ ሕዝቦች፣ እንዲሁም በሁለቱም የቀይ ባሕር ዳርቻ አገራት መካከል ታላቅ የሥልጣኔ አስተዋፅዖ ስታስተናግድ ኖራለች ። አዶሊስ በራስ ገዝ ብቃቷ ገናናውን አክሱማዊ ሥልጣኔን አዋልዳና አሳድጋ አልፋለች። ከእስልምና ሃይማኖት ውልደትና ኃያልነት በተያያዘና ምናልባትም በመጨረሻ በድንገተኛ የውሃ መጥለቅለቅ አደጋ ምክንያቶች ከስማለች። ለአክሱም ሥነመንግሥትና ሥልጣኔ መፋፋም አዱሊስ መሠረታዊ ምክንያት ነበረች። ነገር ግን፣ የአዱሊስና የአክሱም የኢኮኖሚ ዕድገትና ሥልጣኔ ተመሳሳይ ዕድል ገጠማቸው።   

150 BC በአንደኛው ክፍለዘመን  የግሪክና ግብፅ ተወላጁ ኣርቲሜደሮ የተባለ መርከበኛ ነጋዴ፣ “ፐሪፕለስ ኦፍ ዘ ኤርትሪያን ሲ” በተባለው ጥንታዊ መፅሃፉ ላይ ስለ አዱሊስ የፃፈው ታላቅ ታሪካዊ ማስረጃ ሆኖ ይገኛል። መፅሃፉ በአፍሪካ ቀንድ አዱሊስ ብቸኛና አብይ የንግድ ወደብ በመሆን የግብፅ ፋራዕኖች ፍላጎትን ከህንድ፣ ሩቅ ምሥራቅና አፍሪካ ድረስ መጋቢ ወደብ ጭምር እንደነበር ዘግቦታል።እንደ ጣሊያናዊው የከርሰምድር ጥናት ተመራማሪ ከሆነ፣ የአዱሊስ ወደብ ከተማ ከነ ነዋሪዎቿና ጥንታዊ ቅርሷ፣ በ7ኛው ክፍለዘመን ላይ በድንገትና በቅፅበት ከቀይ ባሕር በተነሳ የውሃ ግድግዳ ተጠለቅልቃ ጠፍታለች።  ከቀይ ባሕር ወለል ሥር በድንገትና ሳይገመት በተከሰተተው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት የተፈጠረው ግዙፍ የውሃ ግድግዳ በ6 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን የ አዶሊስ ወደብና ከተማ ከምድረ ገፅ አጠፋት። ይህች ዕጣ ፈንታዋ በአሳዛኝ የተፈጥሮ አደጋ የተወሰነላት ሥፍራ፣ ጥንታዊቷ አዱሊስ ከተማ፣ ብዙ ሺህ ዓመታትን በአፍሪካ ቀንድ ለተከሰተው ሥልጣኔ አብይ የንግድ መናኸሪያ እንደነበረች ለማስታወስ ግብፃውያኑ ፈርዖኖች ከድንጋይ ተሰርቶ የተፃፈበት የአስከሬን ሳጥናቸው ላይ የፑንት ዋና ከተማና የአምላካት ምድር እያሉ እስከዛሬም በቅርሶች ላይ ዘግበውት ያስነብባሉ።    

100 BC የኢኮኖሚያዊ አቋማቸው ከተሻሻለ በኋላ፣ እነዚህ የደቡብ ዓረቢያ ሰፋሪዎች ወደ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ መስፋፋት ይጀምራሉ። አዲሱ ሕዝብ እያደር ከደቡብ ዓረቢያው እናት አገር ቁርኝቱ እየተላለቀ ይመጣና አንድ ራሱን የቻለ፣ የራሱ የሆነ የማህበራዊና የሥልጣኔ አደረጃጀት ያለው ተቋም ሁኖ ይወጣል። ….  ከ1ኛው መክዘ ጀምሮ፣ አዲሱ የዘሮች ውሁድ የሆነው ሕዝብ፣ ከደቡብ ዓረቢያ መንግሥታት ነፃ ሁኖ ራሱን ችሎ መቆም ይጀምራል። የዚህን ሕዝብ ዕድገት የሚገታ አንዳችም ውስጣዊ እንቅፋት አልነበረም፣ የውጪውም ሁኔታ አመች ነበረ። የመልካ ምድራዊ አቀማመጡ አመቺነት ለዚህ አስተዋፅዖ አድርጓል። ምክንያቱም ይህ ቀበሌ በዓረቢያና በመውደቅ ላይ በነበረው የሜሮዔ ንጉሣዊ መንግሥት መካከል ለሚካሄደው ንግድ ዋና አገናኝ አንጓ በመሆን ነው።  *17, የኢትዮጵያ ታሪክ , ባርትኒስኪና ኒየችኮ 2003  


 ከ1ኛው መክዘ ጀምሮ፣ በዛሬይቱ ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰሜናዊ ክፍል፣ ከዓረቢያ የመጡት ሰፋሪዎች የፈጠሩት፣ ልክ በእናት አገራቸው አምሳያ የተደራጀ አንድ ጠቅላይ ግዛት ነበረ። ከክርስቶስ ልደት በፊት አያሌ ምዕተ ዓመታት ቀደም ብሎ ባለው ጊዜ ውስጥ የሚወድቀው ይህ ጠቅላይ ግዛት የተመሠረተበት ወቅት፣ የሳባዊ ዘመን ተብሎ ይታወቃል። ሰፋሪዎቹ በአዲሱ አገር ውስጥ ቀስ በቀስ ጥንካሬ ያገኙትና እንደ አይቀሬነቱም በሥፍራው ያለው ኩሻዊ ሕዝብና ሥልጣኔው ከውጭ ከጎረፈው ከሴማዊው ጋር መቀላቀል የሚጀምረው በዚህን ወቅት ሲሆን፣ የመጤዎቹ ቴክኒካዊ ባህላዊ ሥልጣኔ ደረጃ ከዚህኛው ከፍ ያለ ስል ነበረ፣ በውህደቱ ሂደት ላይ የበላይነቱን ሚና ተጫውቷል። *17, የኢትዮጵያ ታሪክ , ባርትኒስኪና ኒየችኮ 2003  

26 BC አውገስተስ የተባለው የመጀመሪያው የሮም ንጉሠ ነግሥት ሮምን ከዓለም በውበቷ ተወዳዳሪ የሌላት ከተማ አድርጎ ለመሥራት ተነስቶ ሥራ ጀመረ። በጣም ውድና በሥነ ህንፃ ጥበብ የረቀቁ ቤተ ዕምነቶችና፣ በኋላ በማንኛውም የሮም ግዛት ከተሞች የሮማውያን ፎረምስ በመባል የታወቁትን ባለዓይነተኛ ኣርችና ምሶሶ ህዝባዊ ማዕከሎችን አስፋፋ።  እነዚህ ፎረም የተባሉት የከተማ የሕዝብ መሰብሰቢያ ማዕከሎች የሮም ዜጎች የንግድ፣ የዕምነት፣ የፖለቲካ ምርጫ ማካሄጃ፣ ወታደራዊ ድልን ማክበሪያና ጓደኛማቾች የሚገናኙበት ድንቅ ቦታ ነበር። በሮም በዓይነቱ ከሁሉም ያላቀ ጠቀሜታ የነበረው ደግሞ ፎረም ሮማነም ይባል ነበር። በጣም ዕውቅ ከሆኑት የሮማውያን ህንፃ ውስጥ አንዱ፤ ኮሎሲየም የተባለው ስታዲዮም መሳይ የጦረኛና ተጋዳይ አካላት ትዕይንተ መድረክ ነው። ሮማውያን ምርጥ ኃውልቶችንና ባለ ኣርች ህንፃዎችን ገንብተዋል። ኮንክሪት ተጠቅመዋል። ለግዛት ወታደሮቻቸውንና ንግድን ለማሳለጥ ረጂም ዕድሜ ያላቸው መንገዶችን ሠርተዋል፣ ውሃና ፈሳሽን በርቀት ማዳራሻ መንገድ ወይም ከፍ ያለ የውሃ ድልድይ መስመር፣ እንዲሁም የሕዝብ የጋራ ሽንት ቤቶችና የሠውነት መታጠቢያ ክፍሎችን በከተሞቻቸው ሠርተው ነበር።  

በዚያን ጊዜ ቀይ ባህር በከፍተኛ ደረጃ በሄለናዊ (ግሪክ) ሥልጣኔ እቅፍ ውስጥ የሚገኝ ቀበሌ ነበር። ስለዚህም አክሱም ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ ያለው መንግሥት ነበርና ከዚህ ሥልጣኔ ሱታፌ ውጭ አልነበረም። አባ ጰንጠሌዎን ላይ የተገኙት የግርክኛ የደንጊያ ላይ ፅሁፎች፣ የሄለናዊ ሥልጣኔ በዚያን ጊዜ አክሱም ላይ ተስፋፍቶ እንደነበረ አሳማኝ ምስክሮች ናቸው። በወቅቱ አገሪቱን ተዘዋውረው የጎበኙ ግሪኮች በጻፏቸው ድርሳኖች፣ የአክሱም መሪዎች ግሪክኛ ቋንቋን አቀላጥፈው ይናገሩ እንደነበረ ገልጸዋል። የአክሱም ከተማ መልካምድራዊ አቀማመጥ ለሀገረመንግሥት መናገሻነት ምርጫነቷ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል። ከተማዋ ከባህር ወለል 2ሺ ሜትር ገደማ (6,562 ጫማ)፣ በኮረብታ አናት ላይ ትገኛለች። የአየር ንብረት፣ ዝናብ መጠን፣ የለም አፈር ይዞታው እንስሳትንና እርሻን ለማሳለጥ እጅግ ምቹ ነበር። ከሁሉም በበለጠ ጠቃሚነቱ ግን፣ የከተማዋ ስልታዊ አቀማመጥ ቅቡልነት ቁልፍ የሆነ መስቀለኛ የንግድ ዝውውር መስመር ላይ መሆኑ ነው።  አክሱም የባህር ጠረፍን ከውስጣዊው የአፍሪካ ክፍሎች ጋር የምታገናኝ ከፍተኛ የንግድ ማዕከል ሆነች።      

የቅድመ ክርስትናው አክሱማዊ ዘመን፣ ከተቀዳሚው ከሳባዊው ዘመን (አሃዱ አክሱማዊ ተብሎም ይታወቃል) የሚለይባቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ የድርጅታዊ አቋም መጠናከር፣ ራስን የመቻል ብቃት መጨመርና፣ እያንዳንዱ የመጤ ስብስብ ከነባሩ ሕዝብ ጋር ተቀላቅሎ የፈጠረውን የራስን ሥልጣኔ የማዳበር ሂደት ይመጣል። ቀጥሎ አክሱም፣ በመውደቅ ላይ ባለችው በሃብታሟ  ሜሮዔና በዓረብ ባሕረ ሰላጤ መካከል የሚገኝ መንግሥት በመሆኑ ሁኔታው ስላመቸው፣ በኤኮኖሚ ለመበልፀግና በአፍሪካ ምድር ላይ ግዛት ለማስፋት የመብቃቱ፣ በመጨረሻም መንግሥታዊ ሥልጣን በአንድ ተማክሎ፣ መሪዎቹ አክሱምን መቀመጫቸው አድርገው በመቆርቆር ተሰሚነታቸውን ያጠናከሩበት ሁኔታ ታይቷል። *18, የኢትዮጵያ ታሪክ , ባርትኒስኪና ኒየችኮ  

ናፓታና መርዌ ከግብፅ እንደመዋሰናቸው መጠን ቋንቋቸው፣ ፊደላቸው፣ ሃይማኖታቸው ከግብፅ ጋር የተወሰደ ነው። አክሱም ደግሞ ወደፊት እንደምናገኘው ከዐረብ አገር ጋር ጎረቤት ስለሆነ በአክሱም ከነዋሪው በቀር በገዢነት የተመሠረቱት ከደቡብ ዐረብ ከሳባ፣ ከሐበሳት፣ ከሒሚያሪያት የመጡ ነገዶች ስለሆኑ ቋንቋቸው፣ ጽሕፈታቸው፣ ልማዳቸው ከደቡብ ዓረብ የተወረሰ ሆኖ ይገኛል። ደቡብ ዐረብ ደግሞ ይህን አክሱሞች የወረሱትን ሥልጣኔ ከየት አገኘው  ተብሎ ሲመረመር፣ ከባቢሎንና ከአሶር ሆኖ ይገኛል። ይኸውም ማለት ከመካከለኛው ምሥራቅ (አሶር፣ ባቢሎን፣ ከለዳውያን፣ አካድያን) በየጊዜው ከደቡብ ዐረብ መጥተው ሲኖሩ ከዚያ ደግሞ የኤርትራን ባሕር እየተሻገሩ ወደ ኢትዮጵያ ገቡ የነርሱም (የሳባ ፊደል) ፊደልና ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ልማድ ከአሶራውያንና ከአካድ ሲመሳሰል ከናፓታዎችና ከመርዌዎች ከግብፆች ፊደልና ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ልማድ፣ ከአሶራውያንና ከአካድ ሲመሳሰል ከናፓታዎችና ከመርዌዎች፣ ከግብፆች (ሂዩሮግሊፍ) ፊደልና ቋንቋ ጋር በፍፁም የተለያየ ነው። …. *185፣ተክለፃድቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ኑብያ፡አክሱም፡ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት፣ 1951   

ከ5ኛው እስከ 1ኛው መቶ ዓመተ ዓለም አካባቢ ድረስ ያለው ጊዜ፣ ከደቡብ ዓረቢያ ፈልሶ የመጣው ሕዝብ ከእናት አገሩ ጋር ያለውን ጥብቅ ትስስር ጠብቆ ፣ ከአፍሪካ ምድር ጋር መዋህድና ድርጅታዊ ኢኮኖሚያዊ አቋሙን ማጠናከር የጀመረበት ወቅት ነበር። መቀሌ ላይ በተገኘ አንድ የደንጊያ ላይ ፅሁፍ፣ የሳባ የሃይማኖታዊና ዓለማዊ ገዥዎች ይጠሩበት የነበረው “ሙካሪብ” የሚለው የማዕረግ ስም ተጠቅሶ ይገኛል። በበሬ አምሳል ተቀርጾ በዓረቢያ በስፋት ይታወቅ የነበረው አልማካህ (ወይም ኢሉምክ) የተሰኘው የጨረቃ አምላክ፣ በአፍሪካ ምድር ከዋና ዋናዎቹ ዝነኛ አማልዕክት አንዱ ነበር። አጋሜ ውስጥ ለዚህ ጣዖት የቆመ ቤተ ቁርባን፣ ሃውልቲ መላዞ ላይ ደግሞ ቤተ መቅደሱ ተገኝቷል። የሃ ላይ በቁፋሮ የተገኙት ሃውልቶች ፣ በሳባ ዘመነ መንግሥት በዚህ ሥፍራ አንድ ዋና የሃይማኖታዊ ማዕከል ይገኝ እንደነበረ የሚያመለክቱ ናቸው። *16, የኢትዮጵያ ታሪክ , ባርትኒስኪና ኒየችኮ 2003  

የሃ ላይ በቁፋሮ የተገኙት ሃውልቶች፣ በሳባ ዘመነ መንግሥት በዚህ ስፍራ አንድ ዋና የሃይማኖታዊ ማዕከል ይገኝ እንደነበረ የሚያመለክቱ ናቸው። የሃ ላይ ምንም ያህል ያልተበላሸ የሚያምር ቤተ መቅደስ፣ የግድግዳ ስዕሎች፣ የቁርባን ገበታዎች፣ ከጥርብ ደንጋይ የተሠራ የመቃብር ሃውልት ላይ ጽሁፎች ተገኝተዋል። እነዚህ ሁሉ ቅርሶች ትክክለኛ የደቡብ ዓረቢያ ሥነ ጥበብ ገፅታዎች ናቸው። ግን በቁፋሮ የተገኙት ቅሪቶች ብቻ አይደሉም የዚያን ሥልጣኔ ምንነት የሚያረጋግጡት። ሰፋሪዎቹ ለቆረቆሯቸው ከተሞች በሃገራቸው የሚታወቁ ስያሜዎችን ሰጥተዋቸዋል። እስከ አሁንም ድረስ ያለው የሠራዌ (ሠራየ) ከተማ ስያሜ ለዚህ አንድ ምሳሌ ነው። እንደዚሁም ያገሪቱ መታወቂያ የሆነው አቢሲንያ የሚለው ስያሜ፣ በዓረቢያ ከሚታወቅ ሀበሻት ከተባለ የነገድ ስም የመጣ ነው። በተመሳሳይ፣ ግዕዝ የተሰኘው ጥንታዊው የኢትዮጵያ ቋንቋ፣ አጋዚ ከተባለው የሕዝብ ስም የተገኘ ነው። ሌሎችም እንደነዚህ ያሉ በዚያን ጊዜ ከቀይ ባህር ግራና ቀኝ ባለው አገር ይሠራባቸው የነበሩ ብዙ ቃላትና ስያሜዎች አሉ። *16, የኢትዮጵያ ታሪክ , ባርትኒስኪና ኒየችኮ   

አዲሱ የዘሮች ውሁድ የሆነው ሕዝብ፣ ከደቡብ ዓረቢያ መንግሥታት ነፃ ሁኖ ራሱን ችሎ መቆም ይጀምራል። የዚህን ሕዝብ ዕድገት የሚገታ አንዳችም ውስጣዊ ዕንቅፋት አልነበረም፣ የውጭውም ሁኔታ አመች ነበር። …. የኢኮኖሚያዊ አቋማቸው ከተሻ ሻለ በኋላ፣ እነዚህ የደቡብ ዓረቢያ ሰፋሪዎች ወደ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ መስፋፋት ይጀምራሉ። አዲሱ ሕዝብ እያደር ከደቡብ ዓረቢያው እናት አገሩ ቁርኝቱ እየተላቀቀ ይመጣና አንድ ራሱን የቻለ፣ የራሱ የሆነ የማህበራዊና የሥልጣኔ አደረጃጀት ያለው ተቋም ሁኖ ይወጣል።   ከዚህ ወቅት በኋላ፣ ለ አምላክ አልማካህ የሚቆሙ ሃውልቶች የሳባዊው ትክ ክለኛ ቅጂ መሆናቸው ይቀራል። በዚህ ፈንታ፣ ዛሬ የ ኢትዮጵያ መለያ ሁኖ የሚታወቀው የባለሻኛ በሬ ምስል ተተካ። ግዕዝ በ አፍሪካው የቀይ ባሕር ጠረፍ ተውልዶ ያደገና፣ ከሳባዊኛው ጋር የተዛመደ ጽሑፍና ቋንቋ ሲሆን፣ ቀስ በቀስ የሳቢኛውን  ጽሑፍ ተክቶታል። እነዚህ ነገሮች አንድ ራሱን የቻለና አንድ ወጥ የሆነ ሥልጣኔ ለመፈጠሩ ማረጋገጫዎች ናቸው። ካሁን ወዲያ መሪዎቹ ሙካሪብ የሚለውን ስያሜ ትተው፣ ንጉሠ ነገሥት ተብለው መጠራት ጀመሩ።  *17-18, የኢትዮጵያ ታሪክ , ባርትኒስኪና ኒየችኮ 2003    

 

 

Comments are closed.