Page 8

Page 8 – Start 

ከቁፋሮ ግኝቶችና ከዓረብ ባለታሪኮቹ ሥራዎች ለመረዳት እንደሚቻለው፣ በጊዜው ንጉሥ ኤዛና ድል አድርጎ ያበረራቸው የቤጃ ነገዶች፣ በ፰ኛው መክዘ አካባቢ ላይ በሰሜንና በባሕር ጠረፍ ግዛት ዘልቀው ገብተው ነበር። ይህ ወረራ ያለጥርጥር ለአክሱም መዳከም አስተዋፅዖ አድርጓል። 28፣  የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

የባሕር በሩ በእስላም እጅ መውደቁ የመንግሥቱን ኤኮኖሚያዊ መዳከምና የግዛቱን መሸብሸብ አስከትሏል። ከኤኮኖሚያዊ ምንጩ መዳፈን በተጨማሪ የመገንጠል እንቅስቃሴዎች እያየሉ መምጣት፣ መንግሥት በፖለቲካው እንዲዳከም አድርጎታል። በመጨረሻም ማንነታቸውን በውል የማናውቀው ነገዶች የፈፀሙት ተደጋጋሚ ጥቃት ይመጣል። ይሁንና ከዚህ በኋላ ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የክርስቲያናዊው የአክሱም መንግሥት ባህልና ሥልጣኔ በመጉላት ቀጥሏል። ይኸውም ኩሳዊው የአገው ሕዝብ መንግሥታዊ ሥልጣን ሲረከብ የተመሠረትውንና የዛግዌን ሥርወ መንግሥት ለማለት ነው።  29፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

የሕዝብ ስብጥርን በሚመለከት፣ የአክሱም መንግሥት ነዋሪ፣ ከደቡብ ዓረቢያ ፈልሶ የመጣው ሴማዊና፣ በሥፍራው የነበረው ኩሳዊ ሕዝብ ቅልቅል ነው። ሆኖም ግን ከዚያን ወቅት ጀምሮ ሌሎችም ሕዝቦች በመንግሥቱ ውስጥ የጎላ ሚና ሳይጫወቱ አልቀሩም። ከነዚህም ውስጥ የሸዋ፣ የጎጃም፣ የበጌምድር አማራና፣ ከሰሜንም ትግሬ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። ከነባሩ ኩሳዊ ሕዝብ ውስጥ ከቤጃ በቀር፣ በትውፊቱ መሠረት ታሪካዊ ቦታው ላስታ፣ ወይም በትክክል ዋግ የሆነው አገው ይገኛል። በጦረኛነቱ የሚታወቀውና ለነፃነቱ ተቆርቋሪ የሆነው፣ እስከ 17ኛው መክዘ ድረስ ለኢትዮጵያ መሪዎች ራስ ምታት ሁኖባቸው የኖረው የፈላሻ ሕዝብም ምድቡ ከአገው ነው።  

ፈላሾች የሙሴአዊ እምነት (በጥንታዊ ቅርፁ)  ተከታዮችና፣ በይበልጥም በፔንታቶይክ መጽሐፍ ላይ የሚመረኮዙ ሲሆኑ፣ የኋለኞቹን የሚሽናንና የታልሙድን መጻሕፍት አያውቋቸውም። አብዛኞቹ ተመራማሪዎች፣ ፈላሾች አይሁዳዊነትን ተሰደው ከመጡ አይሁዶች የቀሰሙ ያገር ተወላጅ አገዎች ናቸው ብለው ያምናሉ። እነሱ ራሳቸው ግን ተሰድደን ወደ ኢትዮጵያ የገባን እስራዔላውያን ነን ይላሉ።30፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

 የፈላሻ ሕዝቦች እምነታቸውን ይዘው በነፃነት የመኖር ስሜታቸው የራስ ገዝ ፍላጎትና ከአክሱማዊው መንግሥት አፈንጋጭና ተገንጣይ ሊባል የሚችል ትግል ይዘው የቆዩ ናቸው።  ከ9ኛው እስከ 10ኛው መክዘ ባለው ጊዜ ውስጥ በቀውስ ላይ የነበረውን የአክሱምን መንግሥት የመታው፣ በትውፊቱ ፈላሻይቷ ዮዲት በሚል ተይዞ ዝንተ ዓለሙን ሲዘከር የሚኖረው ይኸው ወራሽ የዛጕዌ ኃይል ሳይሆን አይቀርም። የአክሱም መንግሥት የገዥ ክፍሎች ክርስትናን በተቀበሉበት ወቅት፣ የሌላ ዕምነት ተከታዮችን ያሳድዱ እንደነበረ መገመት ይቻላል። በትውፊቱ መሠረት፣ ከውጭ ወረራዎችና ከውስጣዊ ሁከቶች መበራከት የተነሳ እነዚህ ገዥ ክፍሎች ተራቸውን ወደ ሰሜን ሸዋው የአማራ አገር ለመሰደድ ተገድደዋል። የ10ኛው መክዘ ፍፃሜ ሲቃረብ፣ መንግሥቱ እንደገና አንድ ሁኖ እንደነበረ ይታመናል። ግን ከአሁን ወዲያ በላስታው አገው ሕዝብ ወገን በአዲሱ የዛግዌ ሥርወ መንግሥት መሪነት ነው። እሱም የአክሱምን መንግሥት ክርስቲያናዊ ባህሎች ጠብቆ በመቀጠል እስከ 13ኛው መክዘ ሁለተኛ አጋማሽ ድረስ ገዝቷል።   30፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

912 – 1270 AD ዛግዌዎች በምን አኳኋን ሥልጣን እንደያዙም ሆነ ወይም ስለዘመነ መንግሥታቸው ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም። በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው፣ የዛግዌ ሥርወመንግሥት መሪዎች ውስጣዊም ውጫዊም ፖሊሲአቸው እጅጉን በክርስትና እምነት ላይ የተመረኮዘ እንደነበረ ነው። ብዙዎቹ  የዛግዌ ነገሥታትም ቅዱስ የሚለውን የቅፅል ስም ይጠቀሙ ነበር። እጅግ ዝነኛ ከሆኑት ማህል በ1200 ገደማ ላይ መሪ የነበረው ላሊበላ፣ በተጨባጭ ከሃገሪቱ ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ሁኖ ይቆጠራል።

1157 AD ንጉሡ በስሙ በሚጠራው በላሊበላ ከተማ፣ እስከ ዛሬም ድረስ ዝናቸው ያልደበዘዘውን፣ ከአለት ተፈልፍለው የታነፁ አብያተ ክርስቲያን ማሠራቱ ታላቅ የታሪክ ባለውለታ አድርጎታል። ሌሎችም የዛግዌ መሪዎች አብያተ ክርስትያንና ዓለማዊ ህንፃዎችን አሠርተዋል። ነገር ግን የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ናቸው ዛሬ ከነግርማ ሞገሳቸው ቁመው የሚገኙት። በህብረ ቃል ቀመር ብንገልፀው በትክክል በዓለም ካሉት ድንቅ ነገሮች አንዱ ናቸው። አብያተ ክርስቲያኑ በቁጥር 12 ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ትልቁና በጣም የሚያምረው ቤተ መድኃኔ ዓለም ሲሆን፣ (ልኬቱ 33.5ሜ በ23.5ሜ ነው) ሥራውን በአጠቃላይ ያስፈፀመው መሐንዲስ የሲዲ መስቀል አስከሬን በዚህ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳረፈ ይነገራል። የአብያተ ክርስቲያኑ ምሕንድስና የማስጌጫ ሥራዎቻቸው የ አክሱማዊውን ስልት የተከተሉ መሆናቸው በግልፅ ይታያል። ምንም እንኳ አዲሱ መንግሥት ወደ ደቡብ ተሸጋሽጎ ከ አክሱሙ የተለየ ስብጥር ባለው ሕዝብ የሚመራ ቢሆንም፣ የጥንታዊው መንግሥት ሥልጣኔ ወራሽ ነው። ስለዚህም የዝግዌውን የላስታ ሥርወመንግሥት ዘመን፣ አንድነቱ የተጠበቀ መንግሥትና የአንድ ወጥ ሥልጣኔ ታሪካዊ ቅጥያ አድርጎ መመልከት ይቻላል። 33፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

1268 AD በነአኩቶ ለአብ ዘመን አቡነ ተክለሃይማኖት የተባሉ በደብረሊባኖስ፣ አባ ኢየሱስ ሞዓ በሐይቅ ደሴት፣ አባ ዮሃኒስ በደብረ ዳሞ ሆነው በአገሪቱ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ የመንፈሳዊ ህይወት መሪነቱን ቦታ ይዘው ይኖሩ ነበር። በዚያን ጊዜም የዘር ግንዱ ከቀዳማዊ ሚኒሊክ የመጣ ተብሎ የታመነበት ይኩኖ አምላክ የተባለ ወጣት በሸዋ ተጉለት ከተማ ውስጥ ይኖር ነበር። በአቡነ ተክለሃይማኖት የሚመራው የመንፈሳውያኑ ቡድን ይህን ወጣት የሥርወመንግሥት ለውጥ በላስታ በተቀመጠው ንጉሥ ነአኩቶ ለዓብና በተጉለቱ ይኩኖ አምላክ መካከል ሰላማዊና ፈቃደኛነት ላይ የተመሠረተ የሥልጣን ርክክብ እንዲደረግ የቅዱስ ቃል ኪዳን ስምምነት በሚል ሥራ መሥራት ይጀምራሉ። ከብዙ ሥራዎችና ጊዜም በኋላ ንጉሡ ነአኩቶ ለዓብ የእሱ ዘመነ መንግሥት ካለፈ በኋላ ይኩኖ አምላክ መንገስ እንደሚችል ተስማማ። ይህ ስምምነትም ሌሎች ነጥቦችን ጨምሮ የታለመውን ውጤት አመጣ።  

1270 AD ይኩኖ አምላክ ዋና ከተማውን ተጉለት ላይ አድርጎ የሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥትን አስቀጣይነት በማወጅ የኢትዮጵያ ንጉሥ ሆነ። ከዚህን ወቅት አንስቶ የሸዋ አማራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ሚና መጫወት ይጀምራል። የኢትዮጵያ መንግሥት ማዕከል ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ደቡብ ተሽጋሸገ። 37፣የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

ይኩኖ አምላክ ለሥልጣን የበቃው የካህናቱ ሙሉ ድጋፍ ስላልተለየው ነው። የቅዱስ ቃልኪዳን ስምምነቱ ቤተክርስቲያን ለምትሰጠው ድጋፍ አፀፋ፣ በመንግሥት መሬት ላይ የሲሶ ባለመብት እንድት ሆን የሚያደርጋት እንደነበረ ትውፊቱ ያስረዳል። ይህ ብቻ ሳይሆን ዓለማዊውና መንፈሳዊው ኃይሎች በኢትዮጵያ ለወደፊት ለሚኖራቸው የሥልጣን ተደጋጋፊነት ጠንካራ የኤኮኖሚያዊ መሠረት ጥሎአል። ከዚህን ጊዜ አንስቶ ሁለቱም ወገኖች መንግሥታዊ ወሠን የማስፋቱንና ለአዲሶቹ ወገኖች ወንጌል የመስበኩን ተግባር የጋራ ጉዳያቸው አድርገው ያዙት። ይህ የጥቅም ተደጋጋፊነት እስከመንግሥታዊ አስተዳደር ተቋማትም ድረስ የሚዘልቅ ነበር።   35-37፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ ባርትኒስኪና ማንቴል ኒያችኮ፣ 2010

የቅዱስ ቃል ኪዳን ዘመን በመባል የሚታወቀው ወቅት ይኩኖ አምላክ መንግሥታዊ ሥልጣንን ከዛጉዌ ሥርወመንግሥት በቤተ ክርስቲያን በኩል የተፈፀመው ስምምነትን ያመለክታል። ይህ ወቅት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአገሪቱ ውስጥ የሲሶ መሬት ባለቤት እንደ መሆንዋ ካላት ኤኮኖሚያው አቋም የተነሳ ስትጫወተው የኖረች ታላቅ ፖለቲካዊ ሚና ሊጠቀስ የሚገባው ነው። 

በስምምነቱ መሠረት ይኩኖ አምላክ፣ ለአያሌ ምዕተ ዓመታት የዘለቁ ሁለት ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎች በካህናቱ እጅ እንዲያዙ ፈቅዷል። እነሱም የእጨጌውና የአቃቤ ሰዓት ሹመቶች ናቸው። እጨጌው የርዕሰ መነኮሳቱ ቦታ የሱ እንደመሆኑ፣ በመንግሥት ክብረ በዓል ቀን ከመሪው በስተቀኝ ይቀመጣል፣ ይህም በመንግሥቱ ውስጥ ሁለተኛው ሰው መሆኑን ያረጋግጣል። አቃቤ ሰዓት በአንድ በኩል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚነሱ ሃይማኖታዊ ክርክሮችን የማየትና ህጋዊ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ነበረው። የመሪውን የዕለት ተዕለት የሥራ ፕሮግራም እያዘጋጀ ያስፈፅማል።ከጊዜ በኋላ የዚህ ሹም ኃላፊነት ይበልጥ የዓለማዊነት ባህርይ እየተላበሰ መጥቷል።

 

Page 8 – END 

Comments are closed.